Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

አሜሪካ ሱዳንን ሽብርተኝነትን ከሚደግፉ ሃገራት ዝርዝር ውስጥ ሰረዘች

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 5፣ 2013 (ኤፍቢሲ) ሱዳን ሽብርተኝነትን ይደግፋሉ ከሚባሉት ሀገራት ዝርዝር ውስጥ ከዛሬ ጀምሮ መውጣቷ ተገለጸ፡፡

አሜሪካ ከ27 ዓመታት በፊት በሀገር ደረጃ ሱዳን ሽብርተኝነትን ትደግፋለች በሚል በጥቁር መዝገብ ዝርዝሯ ውስጥ ማስፈሯ ይታወሳል፡፡

ይህንንም ተከትሎም ሱዳን ለረዥም ዓመታት ማዕቀብ ውስጥ ቆይታለች፡፡

ባለፉት ወራትም ሁለቱ ሀገራት አዲስ የግንኙነት ምዕራፍ ለመክፈት ውይይቶችን ሲያደርጉ መቆየታቸው የሚታወስ ነው፡፡

ውይይቱን ተከትሎም ሱዳን ከአሜሪካ የጥቁር መዝገብ ለመውጣት ከዚህ ቀደም በኬንያና በታንዛኒያ የአሜሪካ ኤምባሲዎች ላይ ለተፈጸሙ ጥቃቶች 335 ሚሊየን ዶላር ለመክፈል መስማማቷን ይፋ አድርጋለች፡፡

የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክም ሃገራቸው አሜሪካ የጠየቀችው የካሳ ክፍያ መፈጸሟን ገልጸው ነበር፡፡

ይህን ተከትሎም የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፔዮ ሱዳንን ሽብርተኝነትን ይደግፋሉ ከሚባሉ ሃገራት ዝርዝር ለመሰረዝ አሜሪካ ሂደት መጀመሯን መግለጻቸውና ይህም በ45 ቀናት ውስጥ ይጠናቀቃል ማለታቸውም ይታወቃል፡፡

አሁን ላይ የተሰጠው የ45 ቀናት ጊዜ መጠናቀቁን ተከትሎ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ካርቱንም ከዝርዝር መሰረዝ የሚያስችለውን ፊርማ ማኖራቸውን በካርቱም የአሜሪካ ኤምባሲ አስታውቋል፡፡

የአሁኑ የአሜሪካ እርምጃ ለሱዳን ኢኮኖሚ መነቃቃት ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋልም ተብሏል፡፡

ምንጭ፦ ቢቢሲ እና ብሉምበርግ

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version