አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 4 ፣2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የተከዜ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ምንም አይነት ጉዳት እንዳልደረሰበትና ሃይል በማመንጨት ስራ ላይ እንደሚገኝ የጣቢያው ስራ አስኪያጅ ገለጹ፡፡
የጣቢያው ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ከማል አህመድ በስፍራው ለተገኙ ጋዜጠኞች እንደገለጹት፤ ከሰሞኑ መንግስት ከወሰደው ህግ የማስከበር እርምጃ ጋር ተያይዞ ማመንጫው ጉዳት ደርሶበታል መባሉ ሀሰት ነው ፡፡
የተከዜ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ አሁንም ሃይል እያመነጨ መሆኑን ገልጸው፤ በግድቡ ላይ የአውሮፕላን ጥቃት ደርሶበታል የሚለውን ዜና እንደማንኛውም ሰው በድምጸ ወያኔ እና በትግራይ ቴሌቪዢ የሰሙ መሆናቸውን ነው ያስታወቁት፡፡
የተከዜ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ 300 ሜጋ ዋት ሃይል የማመንጨት አቅም ያለው ሲሆን፤ በተጠቃሚ ማነስ ምክንያት አሁን ላይ 225 ሜጋ ዋት እያመነጨ መሆኑን ኢፕድ ዘግቧል፡፡
ጁንታው ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት ከፈጸመ በኋላ ከተከዜ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ የሚመነጨው ሃይል ወደ ብሔራዊ ቋት እንዳይጓዝ በማድረግ ለትግራይ ክልል ብቻ እንዲያገለግል ለማድረግ በክልሉ የሚገኙ ከፍተኛ የሀይል ማስተላለፊያ መስመሮች ላይ ጉዳት ማድረሱንም ገልጸዋል፡፡