አዲስ አበባ ፣ታህሳስ 4 ፣2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ከሳምንታት የኤሌክትሪክ አገልግሎት መቋረጥ በኋላ መቐለ ከተማና አካባቢው ዛሬ አገልግሎት አግኝቷል።
ከአላማጣ ከተማ አንስቶ እስከ መቐለ ድረስ ባሉ ከተሞች በከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር ሽቦዎች (ኮንዳክተሮች) እና ስኒዎች (ኢንሱሌተሮቸ) ላይ የህወሓት ጁንታ ቡድን ባደረሰው ጥቃት በአካባቢዎቹ የኤሌክትሪክ ኃይል ተቋርጦ መቆየቱ ይታወሳል።
በጁንታው ጉዳት የደረሰባቸውን የኤሌክትሪክ ኃይል መሠረተ ልማቶች ጠግኖ ሁሉንም የክልሉ ከተሞች እና የገጠር ቀበሌዎች ኃይል እንዲያገኙ ለማድረግ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ሁለት የጥገና ቡድኖችን አዋቅሮ ቀን ከሌት ሲሰራ ቆይቷል።
በሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ የተሰማራው የጥገና ቡድን በመተማ፣ ሁመራ፣ ወልቃይት እና ማይጨው የሚገኙ የኃይል ማስተላለፊያና ማከፋፈያ ጣቢያዎችን የጥገና ሥራ በማጠናቀቅ ከተሞቹ ኃይል እንዲያገኙ አድርጓል።
ከደሴ በመነሳት ወደሰሜን ምስራቅ ኢትዮጵያ የተሰማራው የጥገና ቡድን ደግሞ ከቀናት በፊት የአላማጣ፣ ማይጨው፣ መኾኒ እና ሰቆጣ ከተሞች ኤሌክትሪክ እንዲያገኙ ያደረገ ሲሆን ዛሬ የመቐለ፣ ኲዊሀ፣ አዲጉዶምና አካባቢው ከተሞች ኤሌክትሪክ እንዲያገኙ ማድረግ ችሏል።
በስፍራው የተሰማሩ የጥገና ባለሙያዎች አስቸጋሪና ፈታኝ ሁኔታዎችን ታግለው ሌት ተቀን በመስራት ለዚህ ውጤት በመድረሳቸው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ አሸብር ባልቻ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
“በፈታኝ ሁኔታ ውስጥ አልፎ ሀገርንና ህዝብን እንደማገልገል የሚያስደስት ነገር እንደማይኖር በተግባር ስላሳያችሁን በሥራችሁ ኮርተናል” ሲሉ የተሰማቸውን ደስታ መግለፃቸውን ኢቢሲ ዘግቧል ።
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል www.youtube.com/fanatelevision ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን