አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 3፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ካቤኔ ከነገ ጀምሮ ወደ ስራ እንደሚገባ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ሙሉ ነጋ አስታወቁ።
የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ሙሉ ነጋ በትግራይ ክልል ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክተው ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም በትግራይ ክልል ሁሉም የመንግስት መስሪያ ቤቶችና የንግድ ድርጅቶች አገልግሎት መስጠት እንዲጀምሩ ከሚለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ጊዜያዊ አስተዳደሩ የአገልግሎት መስጫ ተቋማት ለህዝብ ክፍት እንዲሆኑና ነዋሪዎች ደህንነታቸው ተጠብቆ ወደ እለት ተለት እንቅስቃሴያቸው እንዲመለሱ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ጊዜያዊ አስተዳደሩ የክልሉን ካቤኔ ማዋቀሩን የገለጹት ዶክተር ሙሉ፤ ካቤኔው ከነገ ጀምሮ ወደ ስራ እንደሚገባ አረጋግጠዋል።
በህወሃት ጁንታ ተግባር ተደናግጠው ስራ ያቆሙ የመንግስት ሰራተኞችም ከፊታችን ሰኞ ጀምረው ወደ ስራ ገበታቸው እንዲመለሱ ዶክተር ሙሉ አሳስበዋል።
በተጠቀሰው ቀን ወደ ስራ ገበታው የማይመለስ የመንግስት ሰራተኛ ካለ በገዛ ፈቃዱ ስራውን እንደለቀቀ ተደርጎ እንደሚወሰድም አስገንዝበዋል።
“የመንግስት ሰራተኞች የህዝብ አገልጋይ እንጂ የፖለቲካ ፓርቲ አጀንዳ አስፈጻሚ አይደሉም” ያሉት ዶክተር ሙሉ፤ ሰራተኞች ይህን ተገንዝበው ሙያዊ ግዴታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
መቐለን ጨምሮ አብዛኛው የክልሉ ከተሞች ላይ ሰላምና መራጋጋት መፈጠሩን ጠቁመው፤ “የንግድ ድርጅቶች ከነገ ጀምሮ ወደ መደበኛ ስራቸው መመለስ አለባቸው” ብለዋል።
በተጨማሪም በህጋዊም ሆነ በህገ ወጥ መንገድ የጦር መሳሪያ የታጠቀ ማንኛውም ግለሰብ እስከማክሰኞ ታህሳስ 6 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ ትጥቁን በአቅራቢያው ለሚገኝ የጸጥታ አካል እንዲያስረክብ ዶክተር ሙሉ ማሳሰባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
“ከማክሰኞ በኋላ የቤት ለቤት ፍተሻ እንደሚደረግ ጠቁመው፤ በፍተሻው ትጥቅ የተገኘበት ግለሰብ ሲያጋጥም ተጠያቂ ይሆናል” ብለዋል።
ጊዜያዊ አስተዳዳሩ ክልሉን ወደ ሰላምና መረጋጋት ለመመለስ በሚያደርገው ጥረት ላይ የክልሉ ነዋሪዎች የተለመደ ትብብራቸውን እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል www.youtube.com/fanatelevision ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!