አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 2፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ)በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ተሾመ ቶጋ ከቻይና ረዳት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲንግ ሊ ጋር በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ እና በሁለትዮሽ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡
በውይይቱ የሚሲዮኑ መሪ በትግራይ ክልል በተካሄደው የህግ ማስከበር እርምጃ በተመለከተ ቻይና ያሳየችውን የማይናወጥ አቋም እና በተባበሩት መንግስታት መድረክ ጉዳዩ የኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ መሆኑን በመግለጽ ላሳየችው ድጋፍ ያላቸውን አድናቆት እና ምስጋና ገልጸዋል፡፡
ወንጀለኞችን አድኖ የመያዝና ለህግ የማቅረብ፤ ትግራይን መልሶ የመገንባት፤ በፌደራል መንግስት ክልሉን በጊዜያዊ እንዲመራ የተሰየመው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳዳር ከህዝቡ ጋር ውይይቶችን በማድረግ የማረጋጋት ሥራ የማከናወን፣ የህዝቡን ሠላምና ደህንነት ለማረጋጥ እንዲሁም ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች ሰብአዊ እርዳታ ለማቅረብ በሰላም ሚኒስቴር በኩል ተገቢው ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ረዳት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በበኩላቸው÷ የፌደራል መንግስት በትግራይ ክልል ባለፉት ሳምንታት ባካሄደው ህግ የማስከበር እርምጃ የውጭ ኃይሎች ጣልቃ ለመግባት ያደርጉት ጥረት አግባብነት የሌለው መሆኑንም ገልፀዋል፡፡
ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር ካላት የቆየ ጥብቅ ወዳጅነት እና በሀገሮች የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ያለመግባት መርህ አኳያ የኢትዮጵያ መንግስት ሉአላዊነቱን ባስጠበቀ መልኩ ከሌሎች ጣልቃ ገብነት ነጻ በሆነ ሁኔታ የውስጥ ችግሩን በራሱ ይፈታል የሚል ጽኑ እምነት እንዳላቸውም በአጽኖት ገልጸዋል፡፡
በዚህም መንግስት ትግራይን መልሶ የመገንባት፣ በአፋጣኝ የክልሉን የመንግስት መዋቅር የመመሥረትና እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች እርዳታ ለማድረስ እየተደረገ ያለውን ጥረት ቻይና የምትደግፍ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ሁለቱ ሃገራት ከሁለትዮሽ ግንኙነታቸው በተጨማሪ በአለም አቀፍ መድረኮች በተለያዩ የጋራ ጉዳዮች ላይ የሁለቱን አገራት ጥቅም በሚያስጠብቅ ሁኔታ ለዓለምና ለሰው ልጆች ደህንነት አብረው መስራታቸውን እንደሚቀጥሉ ማረጋገጣቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡