አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 1፤2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በካናዳ የኢፌዴሪ አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ ከካናዳ የጠቅላይ ሚኒስትር የውጭና የመከላከያ ፖሊሲ አማካሪ ዴቪድ ሞሪሰን ጋር ተወያዩ፡፡
በቪዲዮ ኮንፍረንስ በተካሄደው ውይይት አምባሳደር ናሲሴ ስለ ወቅታዊ የኢትዮጵያ ሁኔታ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
አምባሳደሯ የህወሓት ጁንታ የሀገሪቷን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብር መመዝበሩን አንስተዋል፡፡
የጁንታው ቡድን በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የሚካሄደውን አጠቃላይ ሀገራዊ ሪፎርም ለማበላሸት ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡
ቡድኑን ለማስወገድ የተወሰደ የህግ ማስከበር ዘመቻ ንፁሃን ዜጎች ሳይጎዱ በጥንቃቄ መካሄዱን እና መጠናቀቁን አስረድተዋል፡፡
በስፍራው ማህበራዊ ድጋፍ የማቅረብና የመልሶ ማቋቋም ስራ እየተካሄደ ስለ መሆኑም ገልፀዋል፡፡
የተጎዱ መሰረተልማቶችን በፍጥነት ጠግኖ ወደ አገልግሎት ለመመለስ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ወንጀለኛ ቡድኖችን በማደን ወደ ህግ ለማቅረብ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነውም ብለዋል፡፡
ዴቪድ ሞሪሰን በበኩላቸው ስለተደረገላቸው ገለፃ አመስግነው ሀገራቸው ለውጡን ደግፋ የምታግዝ መሆኗን አሳውቀዋል፡፡
አምባሳደር ናሲሴ ካናዳ ለማህበራዊ ድጋፍ ቃል ለገባችው የ3 ሚሊየን የካናዳ ዶላር አመስግነዋል፡፡