አዲስ አበባ፤ ህዳር 30 ፤2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የህወሃት ጁንታ ለግብዣ በሚል ጠርቶ አግቷቸው ከነበሩት የሰሜን እዝ ምክትል አዛዥ ለኦፕሬሽን ብርጋደል ጀነራል አዳምነህ መንገስቴን ጨምሮ 1 ሺህ ያክሉ የሰሜን እዝ የመስመራዊና ከፍተኛ መኮነኖች ተለቀቁ።
የህወሃት ጁንታ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ለግብዣ በሚል ጠርቶ አግቷቸው ከነበሩት የሰሜን እዝ ምክትል አዛዥ ለኦፕሬሽን ብርጋደል ጀነራል አዳምነህ መንገስቴን ጨምሮ 1 ሺህ ያህል የሰሜን እዝ መስመራዊና ከፍተኛ መኮነኖችን የአገር መከላከያ ሰራዊትና የፌዴራል ፖሊስ አባላት በሰሩት የጋራ አሰሳ አስለቀቁ።
የመከላከያ ኢንዶክትሪኔሽን ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጀነራል መሃመድ ተሰማ ለኢዜአ እንደገለጹት የህውሃት ጁንታ ጥቅምት 24 ቀን ምሽት ላይ የእራት ግብዣ ብሎ ከጠራ በኋላ አፍኖ በመውሰድ አግቷቸው ቆይቷል።
የጁንታው ሃይል መስመራዊና ከፍተኛ መኮንኖችን በሸሸበት ቦታ ሁሉ ይዟቸው ሲጓዝ ቆይቶ በቀድሞው የትጥቅ ትግል ወቅት የማዘዣ ቤዝ በነበረው አዴት በሚባል ቦታ አግቷቸው እንደነበርና የጁንታው ታጣቂ ሃይል መደበቁ በአሰሳና በጥናት ተደርሶበታል።
በዚሁ መሰረት የሀገር መከላከያ ሰራዊትና የፌዴራል ፖሊስ ባደረጉት የጋራ አሰሳ እና እርምጃ መስመራዊና ከፍተኛ መኮነኖቹ ምንም ጉዳት ሳይደርስባቸው ከጁንታው አስለቅቀዋል።
ሰራዊቱ ያስለቀቃቸው 1 ሺህ ያክል የመስመራዊና ከፍተኛ መኮነኖች አሁን ላይ ሰራዊቱን መቀላቀላቸውን ሜጀር ጀነራል መሀመድ ገልጸዋል።
ሰራዊቱ ከጁንታው ካስለቀቃቸው መካከል የሰሜን እዝ ምክትል አዛዥ ለኦፕሬሽን ብርጋደል ጀነራል አዳምነህ መንገስቴም ይገኙበታል።
የጁንታውን አባላት የማደን ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን የገለጹት ሜጀር ጀነራል መሀመድ የመጨረሻ ምእራፍ በሆነው ወንጀለኞችን የማደንና የመልሶ ግንባታ ምእራፍ የተደበቀውን ጁንታ አስሶ የመያዙ ስራ በመከላከያ ሰራዊትና በፌዴራል ፖሊስ የጋራ ቅንጅት ተጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል።
ወደፊትም የጁንታውን ቡድንና ወንጀለኞቸን ለህግ የማቅረብና የማደን ስራ ውጤት በየጊዜው ለህዝብ እንደሚገለፅ ጨምረው ገልጸዋል።
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል
https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!