የሀገር ውስጥ ዜና

ዳያስፖራው ለዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ ስለ ሕግ ማስከበር ዘመቻው በማስረዳት ጉልህ አስተዋጽዖ አበርክቷል – የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ

By Abrham Fekede

December 09, 2020

ዳያስፖራው ለዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ ስለ ሕግ ማስከበር ዘመቻው በማስረዳት ጉልህ አስተዋጽዖ አበርክቷል – የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 30፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ዳያስፖራው ሐሰተኛ መረጃዎችን በማጋለጥ ዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ የሕግ ማስከበር ዘመቻውን በትክክል እንዲገነዘብ ጉልህ አስተዋጽዖ ማድረጉን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ አስታወቀ።

ኤጀንሲው ዳያስፖራው ለሠብዓዊ ድጋፍ 80 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ የገንዘብና የዓይነት ድጋፍ ማበርከቱንም ገልጿል።

ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ የተፈፀመውን ጥቃት ተከትሎ በህወሓት ቡድን ላይ የተወሰደው የሕግ ማስከበር ዘመቻ ተጠናቆ ተልዕኮው ወደ ‘ወንጀለኞችን የማደንና የመልሶ ግንባታ ምዕራፍ’ መሸጋገሩ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት ሠራዊቱ ላይ በተፈፀመው ጥቃት የዳያስፖራው ስሜት የነበረው የመደናገጥ፣ የመጨነቅና ስለ ጉዳዩ ማብሪሪያ የመጠየቅ እንደነበር ነው የገለጹት።

ኤጀንሲው ሚሲዮኖችን፣ በውጭ ሀገራት የሚገኙ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማኅበራት፣ በጎ አድራጎት ድርጅቶች ሌሎች የዳያስፖራ አደረጃጀቶችን በመጠቀም የተፈፀመውን ጥቃትና የሕግ ማስከበር ዘመቻውን አስመልክቶ ትክክለኛ መረጃ የማድረስ ስራ መከወኑን ተናግረዋል።

መንግስት ወደ ሕግ ማስከበር እርምጃ የገባበትን ምክንያት በግልጽ በማስረዳት “የህወሓት ቡድን” የተጀመረውን ለውጥ ለማደናቀፍ ሲሰራ የነበረውን ተግባር እንዲገነዘቡት ተደርጓል ብለዋል።

በተለይም በመከላከያ ሠራዊቱ ላይ የደረሰው ጥቃት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የነካ በመሆኑ መንግስት ሕግ ከማስከበር በቀር አማራጭ እንደሌለውና እርምጃው ባይወሰድ በአገር ላይ ይደርስ የነበረውን አደጋ በማስረዳት የእርምጃውን አውድ እንዲያውቁት መደረጉን አብራርተዋል።

ለዳያስፖራው ጉዳዩን እንዲገነዘቡት ብቻ ሳይሆን በሚኖሩበትና በሚሰራባቸው ዓለም አቀፍ ተቋማትና ለዲፕሎማቶች ማብራሪ መስጠታቸውንም ተናግረዋል።

ጥቂት ዳያስፖራዎች የሕግ ማስከበር እርምጃውን በተዛባ መልኩ በመተርጎም የእርስ በእርስ ጦርነት ነው በማለት ዓለም አቀፋዊ ይዘት እንዳለው በማስመስል ዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ለማደናገር ሲሰሩ እንደነበረም ጠቁመዋል።

ይሁንና አብዛኛው የኢትዮጵያ ዳያስፖራ በውስን ዳያስፖራዎች የሚቀርቡ የተዛቡ መረጃዎችን በማጋለጥ ትክክለኛውን መረጃ የማሳወቅ ስራ መስራቱን ገልፀዋል።

በሌላ በኩል ዳያስፖራው ለመከላከያ ሠራዊቱና ለተቸገሩ ወገኖች ሠብዓዊ ድጋፍ ለማድረግ ያሳየው ፍላጎት ከፍተኛ እንደሆነ ነው ዋና ዳይሬክተሯ ያስረዱት።

በሀገር አቀፍ ደረጃ በተቋቋመው ብሔራዊ የድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ ውስጥ ኤጀንሲው የሚመራውና የዳያስፖራውን ድጋፍ የሚያስተባብር ንዑስ ኮሚቴ ተቋቁሞ ወደ ስራ መግባቱን ገልጸዋል።

ዳያስፖራው ልዩነቶች ቢኖሩትም በአገሩ ጉዳይ ያሳየውን አንድነትና ትብብር በማሳደግ አገሪቷን በሚጠቅሙ የልማትና የዕድገት ስራዎች ላይ ተሳትፎውን አጠናክሮ እንዲቀጥል ዋና ዳይሬክተሯ ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።