Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ምክትል ጠ/ሚ ደመቀ መኮንን ለተለያዩ የአፍሪካ ሃገራት አምባሳደሮች በትግራይ ክልል ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ ገለጻ አደረጉ

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 28 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ለተለያዩ የአፍሪካ ሃገራት አምባሳደሮች በትግራይ ክልል ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ ገለጻ አደረጉ።

ሚኒስትሩ ገለጻውን ለጂቡቲ፣ ኤርትራ፣ ኬንያ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ቡሩንዲ፣ ርዋንዳ፣ ኡጋንዳ እና ደቡብ አፍሪካ አምባሳደሮች ነው ያደረጉት።

በዚህ ወቅትም የህወሓት ጁንታ በሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ላይ ጥቃት ከፈጸመ በኋላ መንግስት በክልሉ የወሰደውን ህግ የማስከበር ዘመቻ አምባሳደሮቹና የየሃገራቱ መሪዎች ያሳዩትን ድጋፍ አድንቀዋል።

ደቡብ አፍሪካ እንደ አፍሪካ ህብረት ሊቀ መንበርነቷ በቀጠናው ሰላምን ለማምጣት የምትጫወተው ሚናም የሚደነቅ መሆኑን ተናግረዋል።

ሚኒስትሩ በገለጻቸው ዘመቻው ንጹሃን ላይ የከፋ ጉዳት ሳይደርስ እና መንግስት በክልሉ ህግና ስርአትን ለማስፈን የያዘውን እቅድ ማከናወን በሚያስቸለው አግባብ በፍጥነት መጠናቀቁንም ለአምባሳደሮቹ አስረድተዋል።

አሁን ላይም መንግስት በክልሉ ቴሌኮምን ጨምሮ መሰረተ ልማቶችን፣ የሰብአዊ ድጋፍ ማቅረብ የሚያስችሉ አማራጮችን መዘርጋትና ማረጋገጥ እንዲሁም ከቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን የመመለስ ስራ እያከናወነ መሆኑንም አስረድተዋል።

ከዚህ ባለፈም መንግስት በክልሉ ከተቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑንም አንስተዋል።

አምባሳደሮቹም መንግስት ህግ የማስከበር እርምጃውን ሰላማዊ ዜጎች ላይ ጉዳት ሳይደርስ በፍጥነት በማጠናቀቁ አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

አያይዘውም መንግስት ለተጎዱ ዜጎች ሰብአዊ እርዳታ ለማድረስ የሚያደርገውን ጥረት እንደግፋለንም ብለዋል።

ኢትዮጵያ የቀጠናው “የሰላም መልሕቅ” መሆኗን በመጥቀስም የየሃገራቱ መሪዎች ከኢትዮጵያ መንግስት ጎን እንደሚቆሙ ማረጋገጣቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል www.youtube.com/fanatelevision ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version