Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የበለጸገች እና ሰላሟ የተጠበቀ ትግራይን ለማረጋገጥ ህዝቡ የጀመረውን አስተዋጽኦ አጠናክሮ እንዲቀጥል የብልጽግና ፓርቲ እና ትዴፓ ጠየቁ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 28፣ 2013 (ኤፍቢሲ) የበለጸገች እና ሰላሟ የተጠበቀ ትግራይን ለማረጋገጥ እየተደረገ ያለውን እንቅስቃሴ ለመደገፍ የትግራይ ህዝብ እና ወጣቶች መጫወት የጀመሩትን አስተዋጽኦ አጠናክረው እንዲቀጥሉ የብልጽግና ፓርቲ እና ትዴፓ ጥሪ አቀረቡ።

ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ የነበራቸው በብልጽግና ፓርቲ የትግራይ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ነብዩ ስሁል እና የትዴፓ ዋና ጸሃፊ ግደና መድህን መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ለአመታት የቆየውን የግፈኛውን የህወሓት ቡድን በታኝ አስተምህሮ በማስወገድ ከትግራይ ህዝብ ጋር የበለጠ እጅ ለእጅ መያያዝ ያለበት ጊዜ አሁን ነው ብለዋል።

ከህግ ማስከበር ሂደት ጎን ለጎን ለተጎዱ ዜጎች ሰብዓዊ ድጋፍ ማቅረብ ፤በቡድኑ የወደሙ መሰረተ ልማቶችን በማደስ ዳግም ወደ ስራ ማስገባት እና መሰረታዊ አገልግሎቶችን መልሶ የማስጀምር ስራ መጠናከሩ ሊበረታታ ይገባዋል ብለዋል።

አቶ ነብዩ ስሁል በክልሉ በቅድሚያ ህዝብን የማረጋጋት እና የሰላም ጉዳይ እንዲሁም መሰረተ ልማቶችን ወደቦታቸው የመመለስ ተግባራት በቀዳሚነት እየተተገበረ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህ ውስጥም የአንዳንድ ተቋማት ተነሳሽነት በአቶ ነብዩ በምሳሌነት ተጠቅሷል።

የትምህርት ሚኒስቴር ተጨማሪ 50 ሚሊየን ብር በመመደብ የትምህርት እንቅስቃሴውን ወደ ቀደመው ለመመለስ እየሰራ ነው።

ከ500 ሺህ በላይ የፊት መሸፈኛ ጭምብልም ለዚሁ ተዘጋጅቷል፤ ሌሎችም ተቋማት በተመሳሳይ ርብርብ ላይ ናቸው ሲሉም ነው የገለጹት።

መቐለ ላይ ያሉ ወጣቶችን ጨምሮ ሌሎች አከባቢዎችም በጸጥታ ረገድ ክፍተት እንዳይፈጠር ሀገር ወዳድ መሆናቸውን በተግባር አሳይተዋል ብለዋል አቶ ግደና መድህን።

የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮቹ እንደሚሉት አጥፊውን ቡድን ለማስወገድ ኢትዮጵያውያን ከዳር እስከ ዳር ተሳትፎ አድርገዋል።

ይህ ደግሞ ክልሉን እና ህዝቡን ወደቀደመው ህይወቱ ለመመለስ በሚሰሩ ስራዎች ዳግም መታየት መቻል አለበት ነው ያሉት።

መተባበር ሲኖር ደግሞ በሀሳብ ልዕልና ብቻ የምትመራ ለሁሉም ዜጎቿ እኩል የሆነች ሀገር መፍጠር ቀላል ይሆናል ብለዋል ፖለቲከኞቹ።
 

በአፈወርቅ አለሙ

 

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን

 

 

Exit mobile version