አዲስ አበባ፣ ህዳር 28፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የህወሃት ጸረ ሰላም ሃይሎች የታዳጊ ክልሎችን የተፈጥሮ ሃብት በመውረር እና በመዝረፍ በየአካባቢው የወጣቶች የስራ አጥነት ቁጥር እንዲጨምር አድርገዋል ሲሉ በባህላዊ ወርቅ ዘርፍ የተሰማሩ ማህበራትና የምጣኔ ሃብት ምሁራን ተናገሩ።
ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉት በባህላዊ ወርቅ ዘርፍ የተሰማሩ ማህበራትና የምጣኔ ሃብት ምሁራን ለስራ ፈጠራ በሚል ሰበብ የኔ ለሚሉት አካል ብድርና ማሽነሪ ቅድሚያ በማሰጠትም ማዕድን የሚገኝባቸው መሬቶችን ሁሉ በመውረር የአካባቢው ወጣቶች የበይ ተመልካች ሆነው እንዲቀሩ አደርገዋልም ነው ያሉት።
አቶ አህመድ መሃመድ በቤኒሻንጉል ክልል በአሶሳ ዞን ከስድስት ዓመት በፊት በማህበር በመደራጀት በባህላዊ ወርቅ ምርት ዘርፍ ሲሰማሩ እንደማንኛውም ዜጋ ራሱን ብሎም በማህበሩ የተካተቱ ወገኖቹን ህይወት ለመለወጥ እንደነበረ አስታውሰዋል ።
ይሁንና ከነገ ዛሬ ወደ ስራ አንገባለን በሚል ተስፋ ቢጠባበቁም በዚህ በጸረ ሰላም ሃይሎች በአካባቢያቸው ጂኦሎጂካል ሰርቬይ ጥናት በማስደረግ በርካታ ወርቅ የሚገኝበትን ቦታ የመሬት ወረራ ማድረጋቸው ተገልጿል።
የጸረሰላም ሃይሎች የራሴ የሚሉትን በርካታ አካላት በቦታው ያሰፈሩ ሲሆን በዘመናዊ መሳሪያ ታግዘው ወርቅ እያወጡ መውሰድ መጀመራቸውን ይናገራሉ፡፡
ኢኮኖሚስቱ ረዳት ፕሮፌሰር አሰፋ አዳነ ደግሞ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ወጣቶች በገዛ ሀብታቸው የስራ ዕድል ተጠቃሚ ሳይሆኑ መቅረታቸውን አውስተው በወጣቶች ዘንድ ቅሬታ አንዲፈጠር አድርገዋል ነው የሚሉት።
በክልሉ ይህ በህወሓት የፀረ ሰላም ሃይሎች ሲፈጸም የቆየው የዝርፊያ ተግባር ብቻ ሳይሆን÷ በዚህ አካባቢ ማህበረሰቡ እርስ በአርሱ እንዳይግባባ፣ ጥርጣሬ እንዲፈጠርበት ማድረግ ሌላኛው የሸፍጥ ተግባራቸው ነበር ይላሉ፡፡
የሰመራ ዩኒቨርስቲ ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ሁሴን ኡመር በበኩላቸው÷ በተለይ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በወጣቶች ስራ ፈጠራ ስም የእነዚህ የጸረሰላም ሃይሎች የኔ የሚሉት አካል ብቻ ተጠቃሚ እንዲሆን ተደርጓል ነው ያሉት።
በዚህ መልኩ ባደረጉት ህገ ወጥ ዝርፊያም ባህላዊ የወርቅ አምራቾች ለብሔራዊ ባንክ የሚያቀርቡት ወርቅ ክምችት መቀነሱ በየዓመቱ ይገለጽ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
በዚህ ወቅት የዘርፉን ችግር ለመፍታት ከፖሊሲ ማርቀቅ ጀምሮ የተለያዩ ማሻሻያዎችን ለማድረግ በእቅድ እየተሰራ መሆኑ በማዕድን ሚኒስቴር በኩል በተደጋጋሚ ቢነገርም በወቅቱ መቆጣጠረ አልተቻለም ነበር ነው ያሉት።
በታሪክ አዱኛ