Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የአፍሪካ ኦሊምፒክ ኮሚቴዎች ማኅበር ለጠ/ሚ ዐቢይ የአህጉሩን ከፍተኛ የስፖርት ሽልማት አበረከተ

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 28 ፣ 2013 (ኤፍቢሲ) የአፍሪካ ኦሊምፒክ ኮሚቴዎች ማህበር /አኖካ/ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የአህጉሩን ከፍተኛ የስፖርት ሽልማት /ኦርደር ኦፍ ሜሪት/ አበረከተ።

ሽልማቱ የአፍሪካ ሃገራት መሪዎች ለኦሎምፒክ ስፖርት ማደግ ለሚያበረክቱት አስተዋጽኦ እውቅና የሚሰጥ ነው።

በርካታ የአፍሪካ ሃገራት መሪዎች ይህንን ሽልማት ማግኘት ችለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድም ለኢትዮጵያ ስፖርት ያሳዩት ድጋፍና ለኦሊምፒክ መንደር ግንባታ ያደረጉት የ3 ቢሊየን ብር ድጋፍ ለሽልማት እንዳበቃቸው ተጠቁሟል።

ሽልማቱን ጠቅላይ ሚኒስትሩን በመወከል የባሕልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ካሳው ተቀብለዋል፡፡

በዚሁ ወቅት “ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የስፖርትን ዘርፈ ብዙ ፋይዳ መጠቀም የቻሉ መሪ ናቸው” ሲሉ የባሕልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ካሳው ገልጸዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፕሮጀክት በሆነው የእንጦጦ ፓርክ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ሰፊውን ቦታ እንዲይዙ መደረጉንም ለአብነት ጠቅሰዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለይ ወጣቶች ለስፖርትና ለበጎ አድራጎት ተግባራት ትኩረት እንዲሰጡ አርዓያ በመሆን ጭምር ትልቅ ስራ ማከናወናቸውንም ነው የገለጹት።

የአፍሪካ ኦሊምፒክ ኮሚቴዎች ማህበር ፕሬዚዳንት ሙስጠፋ ቤራፍ በበኩላቸው በቆይታቸው ኢትዮጵያ እንግዳ በማስተናገድ የተካኑ ሕዝቦችን ያቀፈች ታላቅ ሀገር መሆኗን መገንዘባቸውን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ቆይታቸው ለተደረገላቸው እንክብካቤም ምስጋና አቅርበዋል።

በመድረኩ በአዲስ አበባ ለተካሄደው የአፍሪካ ኦሊምፒክ ኮሚቴዎች ማኅበር ጠቅላላ ጉባኤ በስኬት መጠናቀቅ አበርክቶ ለነበራቸው ግለሰቦችና ተቋማት እውቅና መስጠታቸውን ከኢዜአ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን

 

Exit mobile version