አዲስ አበባ ፣ህዳር 26 ፣2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተቀናጀ ለኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምላሽ ለመስጠት ያለመ የሁለት ቀናት የቪዲዮ ኮንፈረንስ ስብሰባ አካሂዷል ፡፡
በውይይቱ በርካታ የዓለም መሪዎች ፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስራ ሃላፊዎች እና ሌሎች የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል ፡፡
በስብሰባው ላይ የተካፈሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን የቪዲዮ መልእክት አስተላልፈዋል ፡፡
አቶ ደመቀ በመልዕክታቸውም ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በዓለም አቀፍ ደረጃ በወረርሽኙ ለተፈጠረው ቀውስ ውጤታማ ምላሽ ለመስጠት ዓለም አቀፋዊ አንድነት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
ለዚህ ስኬት ኢትዮጵያ ቁርጠኛ መሆኗንም አረጋግጠዋል ፡፡
በተጨማሪም እየታየ ላለው የኮቪድ 19 ክትባት አበረታች እድገት እና ተነሳሽነት ኢትዮጵያ ሙሉ ድጋፍ እንደምትሰጥ ገልጸዋል።
ከዚህ ባለፈም ክትባቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለህዝብ ጥቅም እንዲውልና ተመጣጣኝ በሆነ ዋጋ ለሁሉም ተደራሽ መሆን አለበት የሚለውን ዓለም አቀፍ መግባባት ኢትዮጵያ ትደግፋለች ነው ያሉት።
አቶ ደመቀ አያይዘውም ወረርሽኙ ባስከተለው ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖ አፍሪካ የቡድን 20 ሃገራት እዳን በማቃለል እና የእፎይታ ጊዜን በመስጠት ውጤታማ የኢኮኖሚ ማነቃቂያ ፓኬጅ እንዲያቀርቡ ጥሪ ማቅረቧን አስታውሰዋል፡፡
በተጨማሪም ከዚህ ስብሰባ የተባበረ ዓለም አቀፋዊ ምላሽን የሚያነቃቃ እና የሚያስተባብር እንዲሁም ሁሉን አቀፍ፣ ዘላቂ፣ አረንጓዴ እና የማይበገር ሁኔታን ለመፍጠር የሚያስችል እንደሚሆን ያላቸውን እምነት መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።