አዲስ አበባ ፣ ህዳር 26 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በአፍሪካ ደረጃ ነጻ የንግድ ቀጠና መቋቋሙ ለአህጉራዊ የልማት አጀንዳ ስኬት መሪ ተግባር መሆኑን የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ገለጹ።
የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጠና መቋቋምን አስመልክቶ በመሪዎች ደረጃ የቪዲዮ ኮንፈረንስ ውይይት ተካሂዷል።
በውይይቱ ላይ የተሳተፉት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ነጻ የንግድ ቀጠና መቋቋሙ አህጉራዊ ውህደትን ለማሳካት ወሳኝ እርምጃ መሆኑን አንስተዋል።
ፕሬዚዳንቷ የነጻ ንግድ ቀጠናው “ዋነኛ አላማችን የሆነውን አህጉራዊ የውህደት አጀንዳ ለማሳካት ወሳኝ እርምጃ ነው” ብለዋል።
ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ አያይዘውም ኢትዮጵያ ለአህጉራዊ ውህደት አጀንዳ እውን መሆን ያላትን ቁርጠኝነት አረጋግጣለሁ ማለታቸውን ከፕሬዚዳነት ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።