አዲስ አበባ ፣ ህዳር 26 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት ሁለት አመታት በተካሄደዉ የህግ ሪፎርም በተለያዩ የህግ ማዕቀፎች ላይ ማሻሻያዎች መደረጋቸው ተገለፀ፡፡
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የህግና ፍትህ አማካሪ ጉባኤ፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና የፍሬድሪክ ኢበርት ኢንስትቲዩሽን በጋራ ያዘጋጁት የጥናታዊ ጽሁፎች መድረክ በአዲስ አበባ ካፒታል ሆቴል የህግና ፍትህ ማሻሻያ ጉባኤ አባላት እና ምሁራን እንዲሁም የህግ ተማሪዎች በተገኙበት ተካሂዷል፡፡
የጉባኤዉ ዋና ትኩረት እ.ኤ.አ ከ2016 ጀምሮ እየታተመ ለሚገኘው የህግ ጆርናል የተፃፉ የጥናት ጽሁፎች/ አርቲክሎች በማድመጥና በመወያየት ደረጃቸውን የጠበቁ ጽሁፎች ለአንባቢያን እንዲቀርቡ ማድረግ ሲሆን የዚህኛዉ ዓመት ዋና መልእክትም በኢትዮጵያ እየተካሄዱ ባሉ የህግ ማሻሻያዎች ዉስጥ ከነፃነቶች እና መብቶች አጠባበቆች ጋር የተያያዙ ተሞክሮዎች ላይ ትኩረቱን አድርጓል፡፡
በመድረኩ ባለፉት ሁለት አመታት ዉስጥ የተሻሻሉ ህጎችን አስመልክቶ የተፃፉ ፅሁፎች በተለያዩ ፅሁፍ አቅራቢዎች እየቀረቡ ሲሆን በተለይም በነዚህ ዓመታት በተካሄደዉ የህግ ሪፎርም ላይ የንግድ ህግ፣ የወንጀል ሥነ-ሥርዓት ህግና እና የማስረጃ ህግን ጨምሮ ሌሎች በርካታ አዋጆች የተሻሻሉ እና በመሻሻል ሂደት ውስጥ የሚገኙ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በመድረኩ በርካታ ይዘት ያላቸዉ የመወያያ ፅሁፎች በጽሁፍ አቅራቢዎች እየቀረበ ሲሆን የጥላቻ ንግግር ምንነት፣ የሚዲያ ህግ፣ መረጃ የማግኘት መብት እና ሌሎች ከሰብዓዊ መብት ጋር የተያያዙ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ፅሁፎች ቀርበዉ ዉይይት ተደርጎባቸዋል፡፡
የጉባኤዉ ተሳታፊዎች በበኩላቸዉ አማካሪ ጉባኤዉ በሚሻሻሉና በሚረቀቁ ህጎች ዙሪያ እያካሄደ ያለዉ ስራ የሚበረታታና የተሻለ እንደሆነ ገልጸዉ ነገር ግን እነዚህ ህጎችና አዋጆች ከረቀቁ በኋላ አተገባበራቸዉ ላይ ዳሰሳ ማድረግ ላይ እና በሚወጡ ደንብና መመሪያዎች ዙሪያ ጉባኤዉ ያለዉ ሚና በግለፅ መታወቅ ይገባዋል ሲሉ ሀሳብ አስተያየታቸዉን ሰንዝረዋል፡፡
በጠዋቱ መርሀ ግብር የቀረቡ ፅሁፎችን አስመልክቶ ከተሳታፊዎች የቀረቡ ጥያቄዎችና ሀሳቦች ዙሪያ ፅሁፍ አቅራቢዎቹ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን ጉባኤዉ ከስአትም ቀጥሎ ሌሎች ፅሁፎች ቀርበዉ ዉይይት እንደሚደረግባቸው ከጠቅላይ አቃቤ ህግ ያገፕነው መረጃ ያሳያል፡፡
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!