የሀገር ውስጥ ዜና

በኢኮኖሚ ዘርፍ የሚመዘገብ እድገት ለተጨማሪ ድል ያግዛል- የአማራ ክልል ም/ርዕስ መስተዳድር ዶ/ር ፋንታ ማንደፍሮ

By Tibebu Kebede

December 04, 2020

አዲስ አበባ፣ ህዳር 25፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኢኮኖሚ ዘርፍ የሚመዘገብ እድገት ለተጨማሪ ድል እንደሚያግዝ የአማራ ክልል ምክትል ርዕስ መስተዳድር ዶክተር ፋንታ ማንደፍሮ ገለፁ።

በአማራ ክልል የመስኖ ልማት ንቅንቄ በክረምት ወራት የጎርፍ መጥለቅለቅ ከደረሰባቸው ዞኖች በአንዱ በደቡብ ጎንደር ዞን ደራ ወረዳ ተጀምሯል።

ንቅናቄውን ያስጀመሩት የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ፋንታ ማንደፍሮ፥ በሀገር ላይ ያነጣጠረውን ጥቃት ከመመከት በተጨማሪ ኢኮኖሚያዊ እድገትን ለማምጣት ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በኢኮኖሚው ዘርፍ የሚመዘገብ እድገት ለተጨማሪ ድል እንደሚያግዝ ካደጉት ሀገራት መማር እንደሚገባ አሳስበዋል።

“ለሀገራችን አንድነት የማንሰስተውን ድል በኢኮኖሚው ዘርፍ መድገም ካልቻልን በሌሎች እጃችን መጠምዘዙ እንደማይቀር ማሰብ አለብን” ብለዋል። ለዚህም በክልሉ የሚገኘውን ተፈጥሮ ሀብት በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል።

ደቡብ ጎንደር ዞን ደራ ወረዳ ከ1977 ዓ.ም ጀምሮ የሩዝ ምርት እያመረተ ይገኛል፤ ዘመናዊ የአመራረት ስልት ግን እየተከተለ አይደለም፤ በቀጣይ የግብርና ባለሙያዎች እና ተመራማሪዎች ትኩረት ሰጥው ሊሰሩ እንደሚገባ ዶክተር ፋንታ ማንደፍሮ አሳስበዋል።

‘ውኃ በላን’ ሲል የነበረው የአካባቢው ማኅበረስብ ‘ውኃው አበላን’ እንዲል የመስኖ ልማትን ዘመናዊ በማድርግ ምርት እና ምርታማነትን ማሳደግ አለበትም ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ።

የሽንኩርት ክላስተርን በመስኖ በመዝራት የጎርፍ መጥለቅለቅ ያጋጠመውን ኪሳራ ለማካካስ እየተሰራ እንደሆነም አስታውቀዋል።

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር መለስ መኮንን ለአንደኛ ዙር የመስኖ እርሻ ወቅት ውኃ ቆጣቢና ዘመናዊ መስኖ መጠቀም፣ የተሻሻለ ዘር እና የፀረ ተባይ ኬሚካል ለማቅረብ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በአንደኛ እና በሁለተኛ ዙር የመስኖ እርሻ 392 ሺህ 040 ሄክታር ማሳ በማረስ 37 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለማምረት መታቀዱን የቢሮ ኃላፊው ተናግረው፤ ይህም ከባለፈው ዓመት የመስኖ እርሻ ምርት በ23 በመቶ ብልጫ እንዳለው መግለፃቸውንም አብመድ ዘግቧል።

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!