ፋና ስብስብ

100 ኪሎ ግራም ክብደት ማንሳት የቻለው የ11 ዓመቱ ታዳጊ

By Tibebu Kebede

January 01, 2020

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 22፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) 100 ኪሎ ግራም ክብደት ማንሳት የቻለው የ11 ዓመቱ ሩሲያዊ ታዳጊ ብዙዎችን አስገርሟል፡፡

አብዛኛዎቹ ታዳጊዎች ትርፍ ጊዜያቸውን እነደ ቪዲዮ ጌም በመሳሰሉ መጫዎቻዎች ያሳልፋሉ።

ከሩሲያ ገጠራማ ክፍል የተገኘው የ11 ዓመቱ ታዳጊ ቲሞፌይ ክሊቪክን ግን ትርፍ ጊዜውን በአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማዕከል (ጂምናዚየም) ውስጥ የተለያዩ ስፖርቶችን በመስራት ያሳልፋል።

ቲሞፌይ ከአምስት ዓመት ዕድሜው ጀምሮ ክብደት የማንሳት ፍላጎት የጫረበት አባቱ በአካባቢው በሚገኝ ጂምናዚየም ቤት ሲሰራ በመመልከቱ ነበር፡፡

ፍላጎቱን የተመለከተው አባትም ልጁን በጂምናዚየሙ የተለያዩ የክብደት ማንሳት እንቅስቃሴዎችን እንዲሰለጥን እና በውድድሮች እንዲሳተፍ ያበረታታዋል።

በዚህ መሰረትም በስድስት ዓመቱ በአካባቢው በተዘጋጀ ውድድር ላይ በመሳተፍ የ55 ኪሎግራም ክብደት በማንሳት በእድሜ የሚበልጡትን ተወዳዳሪዎች በማሸነፍ ዳኞችን ማስገረም ችሏል።

የ11 ዓመቱ ታዳጊ ቲሞፌይ ክሊቪክን በቅርቡ በቼሊያ ቢኒስክ በተካሄደው የክብደት ማንሳት ውድድርም 100 ኪሎ ግራም ክብደት ማንሳት መቻሉ ተነግሯል።

በቀጣይም 105 ኪሎግራም ክብደት በማንሳት ስሙን በዓለም ድንቃድንቅ መዝገብ ላይ ለማስፈር ዝግጅት እያደረገ መሆኑ ተመላክቷል።

ምንጭ፣ ኦዲቲ ሴንትራል