አዲስ አበባ፣ ህዳር 25፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በምስራቅ ሸዋ ዞን አዳሚ ቱሉ ወረዳ በደረሰ የትራፊክ አደጋ የሰባት ሰዎች ህይወት ማለፉን ፖሊስ አስታወቀ።
አደጋው በድሎ ሬጴ ቀበሌ ውስጥ ትናንት ማምሻውን መድረሱን የዞኑ ፖሊስ መምሪያ የኮሙዩኒኬሽንናና ሚዲያ ሃላፊ ኮማንደር አስቻለው አለሙ ተናግረዋል፡፡
በዚህም አሽከርካሪውን ጨምሮ የሰባት ሰዎች ህይወት ወደያውኑ ማለፉን አስታውቀዋል፡፡ አደጋው የደረሰው ከቡታ ጅራ ወደ ባቱ እየተጓዘ የነበረ ሚኒባስ የህዝብ ማመላለሻ 16 ሰዎች ጭኖ በፍጥነት ሲጓዝ በመገልበጡ መሆኑን ኮማንደር አስቻለው መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በአደጋው ህይወታቸው ካለፈ ሰዎች በተጨማሪ አምስት ሰዎች ላይ ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶ በአዳማ ሆስፒታል የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው እንደሚገኝ ተናግረዋል።