ዓለምአቀፋዊ ዜና

አሜሪካ ተጨማሪ 750 ወታደሮችን በመካከለኛው ምስራቅ ልታሰማራ ነው

By Tibebu Kebede

January 01, 2020

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 22፣ 2012(ኤፍ ቢ ሲ) አሜሪካ ባግዳድ የሚገኘው ኤምባሲዋ በሰልፈኞች ጥቃት ከደረሰበት በኋላ ተጨማሪ ወታደሮችን ወደ መካከለኛው ምስራቅ ልታሰማራ መሆኑን አስታውቃለች።

አሜሪካ ባሳለፍነው እሁድ ዕለት በኢራን እንሚደገፉ በሚነገርላቸው እና በኢራቅ በሚንቀሳቀሱ የሂዝቦላህ ታጣቂዎች ላይ በፈጸመችው የአየር ጥቃት 25 የቡድኑ አባላት ህይወት ማለፉ ይታወሳል።

ይህን ተከትሎም የኢራቅ ተቃዋሚዎች በትናንትናው ዕለት ባግዳድ በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ላይ ጥቃት ሰንዝረዋል።

የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ማርክ ስፔር ጥቃቱን ተከትሎ አሜሪካ 750 የሚደርሱ ወታደሮችን በመካከለኛው ምስራቅ ልታሰማራ መሆኑን አስታውቀዋል።

በቅርቡ ተጨማሪ ወታደሮች ወደ ስፍራው ይላካሉ ያሉት ሚኒስተሩ፥ ይህም በኢራቅ የሚገኙ የአሜሪካ ሰራተኞች እና ንብረቶች ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመከላከል እንደሚያስችል ገልጸዋል።

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው ለተፈጠረው ጥፋት ቴህራን ሙሉ ሃላፊነቱን እንደምትወስድ ተናግረዋል።

በተጨማሪም ኢራቅ ኤምባሲውን ለመጠበቅ ኃይሏን እንደምትጠቀም እንጠብቃለን፤ ይህንንም እንዲያውቁ አድርገናል ብለዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማይክ ፖምፒዮ ጥቃቱ በአሽባሪዎች አቀናባሪነት የተፈጸመ መሆኑን ጠቁመዋል።

ምንጭ፡-አልጀዚራ