Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የብሔራዊ መታወቂያ ዝግጅት ወደ ተግባር መግባት እንዳለበት ተጠቆመ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 24፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የብሔራዊ መታወቂያ ዝግጅት ወደ ተግባር መግባት እንዳለበት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለፀ።

ቋሚ ኮሚቴው የሰላም ሚኒስቴርንና ተጠሪ ተቋማቱን የ2013 በጀት ዓመት ዕቅድና የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አፈጻጸም በገመገመበት ወቅት ነው ይህንን መግለፁን ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የብሔራዊ መታወቂያ ዝግጅትን በተመለከተ ከሂደት ባለፈ ወደ ተጨባጭ ተግባር አለመግባቱን የሰላም ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ብርቱካን ሰብስቤ ገልጸዋል።

የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል በዚሁ ወቅት፥ የብሔራዊ መታወቂያ የሙከራ ትግበራ መደረጉን አንስተው፤ እስካሁን ያሉ እንቅስቃሴዎች ለ30 ሚሊየን ዜጎች መታወቂያ ማተም የሚያስችሉ መሆናቸውን ነው ያብራሩት።

በህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዙሪያ የተሰሩ ስራዎችንም የገመገመው ቋሚ ኮሚቴው፤ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት በማሳተፍ  ሕገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርን ለመቆጣጠርና ለመከታተል የሚያስችል የሶፍትዌር ቴክኖሎጂ በሰላም ሚኒስትር እና በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን መሪነት ስራ መጀመሩ በጥንካሬ አንስቶታል።

ከዚህ ጋር በተያያዘም የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪሃት፥ ሕገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርን ለመቆጣር የወጣውን አዋጅ መሰረት በማድረግ ደንብና መመሪያ መዘጋጀቱን ገልፀዋል።

ሁሉም መሳሪያዎች የመንግስትን ጨምሮ መመዝገብና በስርአት መመራት እንዳለባቸውም አብራርተዋል።

የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ጀኔራል አቶ መላኩ ፋንታ፥ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ ክልሎች ከ700 በላይ በወንጀል ተጠርጣሪዎች ከ500 በላይ የነፍስ ወከፍና የቡድን መሳሪያዎች እንዲሁም ከ14 ሺህ በላይ ጥይቶች መያዛቸውን ገልጸዋል።

ቋሚ ኮሚቴው በኦዲት ዙሪያ የተሰሩ ስራዎችንም የገመገመ ሲሆን፥ በዚህም የ2012 ዓ.ም በጀት ዓመት የኦዲት ግኝትን በተመለከተ በፌዴራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት በኩል እንዲስተካከሉ የተባሉ የኦዲት ግኝቶች ላይ የተወሰደው እርምጃ ዝርዝር ሪፖርት አለመቅረቡን ሰብሳቢዋ በውስንነት ጠቅሰዋል።

በግምገማው በሀገራዊ የጋራ ታሪክ፣ ትርክትና መገለጫዎቹ እንዲሁም በህገ መንግስቱ መሰረታዊ መርሆች ላይ ብሄራዊ መግባባት ለመጀመር እና አለመግባባቶች ግጭት አልባ በሆነ ግንኙነት እንዲፈቱ መከላከል የሚያስችል ስትራቴጂክ ሰነድ መዘጋጀቱን ቋሚ ኮሚቴው በጥንካሬ አንስቷል።

ብሔራዊ መግባባትን አስመልክቶ በሩብ አመቱ የተፈጸመው ከታቀደው 42 በመቶ ብቻ መሆኑንም ወይዘሮ ብርቱካን በጉድለት አንስተዋል።

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version