አዲስ አበባ፣ ህዳር 23፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ የጎርጎርዮስ አደባባይ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በፈነዳው ቦምብ ምንም የደረሰ ጉዳት አለመኖሩን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
ቦምቡ በቦሌ ክፍለ ከተማ ልዩ ቦታው ጎርጎርዮስ አደባባይ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሚገኝ አንድ የቆሻሻ መጣያ ገንዳ ውስጥ ተጥሎ መገኘቱን ኮሚሽኑ ጠቅሷል፡፡
በዚህም ከአካባቢው ሰዎች በደረሰው ጥቆማ የፈንጅ አምካኝ ባለሙያዎች በማለዳ ወደ ስፍራው በማቅናት ለማምከን ባደረገው ሙከራ ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ ሊፈነዳ መቻሉን ነው ኮሚሽኑ ያስታወቀው፡፡
በዚህም አንድ ግለሰብ በፍንጣሪው ቀላል ጉዳት የደረሰበት ሲሆን ተጎጂው የህክምና እርዳታ በማግኘት ወደ ቤቱ ተመልሷል፡፡
በተመሳሳይ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 ልዩ ቦታው ጉርድ ሾላ ቅዱስ ያሬድ ሆስፒታል ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ለፖሊስ በደረሰ መረጃ መሰረት ባለሙያዎች ቦታው ድረስ በመገኘት ቦምቡን ማምከናቸውን ነው ኮሚሽኑ የገለጸው፡፡
ፖሊስ ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት ባላቸው ግለሰቦችና አጠቃላይ የምርመራውን ውጤት እንደሚያሳውቅ አስታውቋል፡፡
ኮሚሽኑ ህብረተሰቡ ከፖሊስ ጋር የሚኖረውን የመረጃ ልውውጥ በማጠናከር አካባቢውን በንቃት እንዲጠብቅ ጥሪ ማቅረቡን ከመዲናዋ ፖሊስ ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡