አዲስ አበባ፣ ህዳር 23፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በትግራይ ክልል እየተካሄደ ያለውን ህግን የማስከበር ዘመቻ አስመልክቶ በአሜሪካ የኢትዮጽያ አምባሳደር ፍጹም አረጋ ገለጻ አድርገዋል።
አምባሳደር ፍጹም በዚሁ ወቅት እንዳሉት ጽንፈኛው የህወሓት ቡድን ባለፉት ሁለት አመታት መንግስት ለሰላም እና ለፖለቲካ ውይይት ያደረጋቸውን በርካታ ጥረቶች ባለመቀበል የተጀመረውን ለውጥ ለማደናቀፍ ሲሰራ ቆይቷል።
ቅንጣት ሰብዓዊነት የማያውቀው ይሄው ቡድን ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ምሽት ላይ በአገር መከላከያ ሰራዊት የሰሜን እዝ ላይ የፈጸመው እጅግ አረመኒያዊ ጥቃትና ዝርፊያ ሳቢያ መንግስት ተገዶ ህግ ወደ ማስከበር እርምጃ መግባቱን ተናግረዋል።
ህግ የማስከበር ዘመቻው በስኬት መጠናቀቁን ገልጸው፤ ቀሪው ተግባር በፌደራል ፖሊስ በኩል የወንጀለኛውን ቡድን በቁጥጥር ስር ማዋልና በህግ እንዲጠየቁ ማቅረብ ነው ብለዋል።
ጎረቤት አገራት በዚህ ወሳኝ ወቅት የኢትዮጵያን ሉዓላዊ አንድነት በማክበር ላሳዩት አጋርነትና ወዳጅነት አምባሳደር ፍጹም አመስግነዋል።
በገለጻው የተሳተፉ አምባሳደሮችም ኢትዮጵያ ለቀጣናው ያላትን የማይተካ ሚና በመጥቀስ፤ መንግስት ህግ የማስክበር ዘመቻውን ንጹሃን ሳይጎዱ በአጭር ጊዜ በማጠናቀቁ አድናቆታቸውን ገልጸዋል፡፡
በቀጣናው ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ተቀራርቦ ለመስራት አምባሳደሮቹ መስማማታቸውን በዋሺንግተን ዲሲ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።