አዲስ አበባ ፣ህዳር 22 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በህግ የሚፈለጉ የጁንታውን ቡድን አባላት ከማደኑ ጎን ለጎን የትግራይን ክልል ወደ መደበኛው ስርዓት ለመመለስ የሚያስችሉ ስራዎችን ተግባራዊ እያደረጉ መሄድ እንደሚገባ ምሁራን ተናገሩ፡፡
ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ያነጋገራቸው ምሁራን በክልሉ በጁንታው የወደሙ መሰረተ ልማቶችን መጠገን፣ የፀጥታ ሀይሎችን ሪፎርም ማድረግ እና ተቆርጠው የቀሩ ታጣቂዎችን ትጥቅ ማስፈታት ቀዳሚ ስራ መሆን አለበት ብለዋል።
በጅማ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምሁሩ ረዳት ፕሮፌሰር አብዮት ደስታ እንዳሉት÷ አሁን የትግራይ ህዝብ እፎታይ የሚያገኝበት አንድ ምዕራፍ መጀመሩን የሃገር መከላከያ ስራዊት መቐለን በመቆጣጠር አብስሯል፡፡
አሁን የተገኘው እፎይታ ቀጣይነት እንዲኖረውም መንግስት የማረጋጋቱን ስራ በሚገባ ማከናወን እንዳለበት የሚያነሱት ረዳት ፕሮፌሰሩ ህዝቡ ከሃገር መከላከያ ሰራዊት አባላት እና ከፖሊስ ጋር እጅና ጓንት ሆኖ መስራት ይጠበቅበታል ብለዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰላም እና ደንህነት ተቋም መምህርና ተመራማሪው ዶክተር ዮናስ አደይ በበኩላቸው÷ ህዝቡ ለጥቂት ግለሰቦች ተጨማሪ ዋጋ መክፈል እንደማይገባው በመጥቀስ የጁንታውን ቡድን አባላት ለህግ ለማቅረብ በሚደረገው ጥረት ላይ ሚናውን ሊጫወት ይገባልም ነው ያሉት።
በሌላ በኩል በህግ ማስከበሩ ሂደት ውደመት የደረሰባቸው የአገልግሎት መስጫ ተቋማትን በፍጥነት ወደ ስራ በማስገባት የህዝቡ የዕለት ከዕለት ህይወት እንዲቀጥል ማድረግም አሁን ላይ ከመንግስት ይጠበቃል ብለዋል።
በተጨማሪም በፅንፈኛው ቡድን የታጠቁ ሀይሎችን ትጥቅ በማስፈታት ለመልሶ ማገገሚያ የሚሆኑ የተሃድሶ ማዕከላትን በማቋቋም እንዲገቡ በማድረግ ለሰላም ግንባታው ሚና እንዲጫወቱ ማድረግ ይገባልም ብለዋል ምሁራኑ።
አሁንም ቢሆን የጁንታው ቡድን አባላት እጃቸውን ለፖሊስ ለመስጠት ጊዜው አልረፈደም የሚሉት ምሁራኑ ይህን በማድረግ ለትውልድ እና ለታሪክ ትምህርት የሚሆን ነገር ሰርተው ማለፍ እንደሚኖርባቸው አንስተዋል።
በበላይ ተስፋዬ