አዲስ አበባ፣ ህዳር 21፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) መንግስት በስደት ሱዳን የሚገኙ ዜጎችን በትግራይ ክልል መልሶ የማቋቋም ስራ እየሰራ መሆኑን በጠቅላይ ሚኒስትር ፅሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ማዕከል ግንባታ ሚኒስትር አቶ ዛዲግ አብርሃ ገለጹ።
አቶ ዛዲግ ህወሓት በትግራይ ቴሌኮምን ጨምሮ በርካታ የመሰረተ ልማቶችን በማውደም የትግራይ ህዝብን ከተቀረው ዓለም ጋር እንዳይገናኝ ስለማድረጉ አብራርተዋል።
የሀገር መከላከያ ሰራዊት መቐለ መግባቱን ተከትሎ ባለሙያዎች የስልክ መስመሮችን ለማስተካከልና ግንኙነቱን ለማስጀመር እየሰሩ መሆኑንም አብራርተዋል።
የህወሓት ቡድን በክልሉ አውሮፕላን ማረፊያዎችን ጨምሮ መንገዶችንና ድልድዮችን ማፈራረሱን ገልጸዋል።
አሁን መንግስት እነዚህን መሰረተ ልማቶች መልሶ እየገነባ መሆኑን ኢዜአ የጀርመን ድምጽ የቴሌቪዥን ጣቢያን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡
አቶ ዛዲግ የኢትዮጵያ መንግስት ሁሉንም ነገሮች በግልጽ የሚያደርግና ምንም የሚደበቅ ነገር እንደሌለውም ነው ያስረዱት።
ዓለም አቀፍ ስደተኞችን በማስተናገድ ኢትዮጵያ ከዓለም ሶስተኛዋ ሃገር በመሆኗ ሰብዓዊ እርዳታዎችን እንዴት ማሰራጨት እንዳለባት ጠንቅቃ ታውቃለችም ብለዋል።
የተበላሹ መሰረተ ልማቶችን በማስተካከል ወደ ሱዳን የተሰደዱ ዜጎችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ቀደመ ኑሯቸው ለመመለስ ቀንና ሊ እየተሰራ መሆኑን ነው ያስረዱት።