አዲስ አበባ፣ ህዳር 21፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ከደብረ ማርቆስ ሪፈራል ሆስፒታል ህጻን የሰረቀችው ግለሠብ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ዋለች።
በደብረ ማርቆስ ሪፈራል ሆስፒታል ከስናን ወረዳ ሆስፒታል አንድ ልጅ ወልዳ አንደኛውን ለመውለድ ያልቻለችው እናት ህጻን ሰርቃለች፡፡
ግለሠቧ ሆስፒታሉ ውስጥ የነበረን ህጻን የታቀፈ አባትን አዛኝ መስላ በመጠጋትና ህጻኑን በመያዝ ላግዝህ ብላ ከተቀበለች በኋላ እቃ እንዲያመጣላት በማዘዝ እቃውን ሊያመጣላት ሲሄድ ህጻኑን ይዛ መሠወሯ ነው የተነገረው።
ይህ መረጃም ለከተማዋ ፖሊስ መድረሱን ተከትሎ ከደብረ ማርቆስ ሪፈራል ሆስፒታል በመሰብሰብ እና በመተንተን ጉዳዩ በአንድ ተጠርጣሪ ላይ ማረፉን የከተማዋ የወንጀል ምርመራ ክፍል ሀላፊ ምክትል ኮማንደር መሀሪ አለማየሁ ገልፀዋል።
ተጠርጣሪዋ ህዳር 13 ቀን 2013 ዓ,ም ለመውለድ ከደጀን ወረዳ ደብረ ማርቆስ ሪፈራል ሆስፒታል ገብታ በሠላም ተገላግላ ወደ መኖሪያ አካባቢዋ ተመልሳለች፡፡
ህዳር 18 ቀን 2013 ዓ.ም ግን ልጇ በመታመሙ ለህክምና ተመልሳ ደብረ ማርቆስ ሪፈራል ሆስፒታል የመጣች ቢሆንም የልጇ ህይወት አልፏል። ህይወቱ ያለፈውን ልጇንም ሽንት ቤት በመክተት ወደ ማዋለጃ ክፍል በመሄድ አጋጣሚውን ተጠቅማ አቶ ስማቸው የኔአለም ታቅፎት የነበረውን ህጻን ይዛ መጥፋቷን ፖሊስ ገልጿል።
ፖሊስም ባደረገው ያልተቋረጠ ክትትል በደብረ ማርቆስ ከተማ ቀበሌ 10 ከወንድሟ ቤት ልጁን እንደያዘች መገኘቷን ከአማራ ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
በተጠርጣሪዋ ላይም ምርመራ እየተደረገ መሆኑን የምርመራ ክፍል ሀላፊው ገልጸዋል።