አዲስ አበባ፣ ህዳር 21፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የራያ ግንባር አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ባጫ ደበሌ በህወሓት ታጣቂ ቡድን ንብረታቸው የተዘረፈባቸውና ተፈናቅለው በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ተጎጂዎችን በመጎብኘት ድጋፍ አደረጉ።
ሌተናል ጄኔራል ባጫ ደበሌ በራያ ግንባር ታጣቂ ቡድኑ ውድመት ባስከተለባቸው አካባቢዎች ተዘዋውረው ህብረተሰቡን አነጋግረዋል፡፡
በዚሁ ወቅትም ፅንፈኛው ቡድን በአካባቢው መሰረተ ልማቶችን ከማውደሙ ባሻገር የህዝብን ንብረት እያወደመና እየዘረፈ መሸሹን ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።
በአካባቢው በመከላከያ ሰራዊት ጥቃት እየደረሰበት ሲሸሽ የከረመው ሀይልም የአርሶአደሩን እህል እያግበሰበሰ መጥፋቱንም ነዋሪዎቹ አስረድተዋል።
አሁን ቀዳሚ ተግባራችን ህብረተሰቡን ማቋቋምና መደገፍ ነው ያሉት ሌተናል ጄኔራል ባጫ ደበሌ፥ ለአባወራዎቹ የገንዘብ ድጋፍ አበርክተዋል።
በተያያዘ ዜና ሌተና ጄኔራል ባጫ ደበሌ ህግን በማስከበር ግዳጅ ላይ ተሰማርተው ጉዳት የደረሰባቸውን የመከላከያ ሰራዊት፣ የአማራ ልዩ ሀይልና ሚሊሻ አባላት በሆስፒታል ተገኝተው ጎብኝተዋል።
በወልዲያ ሆስፒታል የተገኙት ሌተናል ጄኔራል ባጫ ደበሌ፥ ወታደሮቹን ተዘዋውረው ከጠየቁ በኋላ የምስጋናና የማነቃቂያ ንግግር አድርገዋል።
ኢትዮጵያ በተለያዩ ወቅቶች ከወራሪ ሀይል ጋር መግጠሟን ያስታወሱት ሌተናል ጄኔራል ባጫ ደበሌ፤ አንድም ጊዜ ግን ኢትዮጵያን መከፋፈል አልቻሉም ብለዋል።
“አሁንም የተነሳብን የገጠመን የውስጥ ወራሪ ነው ፍላጎቱም ኢትዮጵያን መከፋፈል ነው፤ ይሄ ግን እውን የሚሆነው የእኛን ሬሳ ተራምደው ሲያልፉ ብቻ ነው” ብለዋል።
“እናንተ ደማችሁን ያፈሰሳችሁበትን፣ አጥንታችሁን የከሰከሳችሁትን ጓዶቻችሁን የቀበራችሁለትን ዘመቻ በቶሎ አገግማችሁ መቐለ ላይ በጋራ እናከብረዋለን”ም ነው ያሉት።
በህግ ማስከበር ዘመቻ ላይ ተሳትፈው ጉዳት የደረሰባቸው የሰራዊቱ አባላትም በአጭር ጊዜ አገግመው በግዳጅ ላይ ያለውን ሀይል ተቀላቅለው የልፋታቸውን ውጤት ማየት እንዳለባቸው ለሰራዊቱ ተናግረዋል።
በኃይለሚካኤል ዴቢሳ