ስፓርት

ሴኔጋላዊው አማካይ ፓፓ ቦባ ዲዮፕ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ

By Tibebu Kebede

November 30, 2020

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 20 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ሴኔጋላዊው አማካይ ፓፓ ቦባ ዲዮፕ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ።

ዲዮፕ በ42 አመቱ ከዚህ ዓለም በሞት መለየቱን ቢቢሲ ዘግቧል።

አማካዩ ረዘም ላለ ጊዜ በነበረበት በሽታ ምክንያት ህይወቱ ማለፉም ነው የተሰማው።

ቦባ ዲዮፕ በፈረንጆቹ 2002 የዓለም ዋንጫ የማይረሳ ጊዜ ያሳለፈው የሴኔጋል ብሄራዊ ቡድን አባልና ከወሳኝ ተጫዋቾች መካከል አንደኛው እንደነበር የሚታወስ ነው።

በወቅቱ ሃገሩ ሴኔጋል በውድድሩ ሩብ ፍጻሜ ድረስ ላደረገችው ጉዞ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጉም አይዘነጋም።

ከዚህ ባለፈም በውድድሩ ሴኔጋል ከፈረንሳይ ጋር ባደረገችው የምድቡ የመክፈቻ ጨዋታ ብቸኛዋንና የማሸነፊዋን ጎል በማስቆጠር ባለ ታሪክም ነበር።

ዲዮፕ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ፖርትስማውዝና ፉልሃምን ጨምሮ በሌሎች ክለቦች በነበረው ቆይታ ከ120 በላይ ጨዋታዎችን አድርጓል።

በፈረንጆቹ 2008 በሃሪ ሬድናፕ ከሚሰለጥነው ፖርትስማውዝ ጋር የኤፍ ኤ ካፕ ዋንጫ ያሸነፈው ቡድንም አባል እንደነበር ይታወሳል።