የሀገር ውስጥ ዜና

በአዲስ አበባ ከተማ በጎዴ  እና በአሶሳ ከተሞች ስም ትምህርት ቤቶች ተሰየሙ

By Tibebu Kebede

November 29, 2020

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 20 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ በሶማሌ ክልል ከተማዋ ጎዴ  እና በቤንሻንጉል ጉሙዝ ዋና ከተማ አሶሳ ስም ትምህርት ቤቶች ተሰየሙ።

ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ከሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ መሀመድ ፣የአዲሰ አበባ ምክር ቤት አፈጉባዔ  ወይዘሮ ዘርፈሽዋል ንጉሴ  እና  በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት አፈጉባኤ አቶ ታደለ ተረፈ እና ሌሎች ከፍተኛ  አመራሮች በትምህርት  ቤቶቹ በመገኘት በይፋ ሰይመዋል ።

ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ እንደገለፁት የትምህርት ቤቶቹ ስያሜ ዋናው አላማ የቀጣዩ ትውልድ የብሄር ብሄረሰቦችን እሴት እና ባህል ተገንዝበው በአብሮነት እና በአንድነት እርስ በእርስ ለመቀራረብ መሆኑን ተናግረዋል ።

ዛሬ ስያሜ የተሰጣቸው ትምህርት ቤቶች የክልሎቹን ባህል፣ማንነት እና ታሪክ በሚያንፀባርቁ መንገድ እንዲገነቡ እና እንዲደራጁ ይደረጋል ብለዋል ወይዘሮ አዳነች ።

የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ መሀመድ  እና የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት አፈጉባኤ አቶ ታደለ ተረፈ የሁሉም ከተማ በሆነችው አዲስ አበባ በክልላቸው ካሉ ከተሞች ስም ትምህርት ቤት መሰየሙ እንዳስደሰታቸው ገልፀዋል

የክልላቸውን ባህል ፣ማንነት እና ታሪክ የሚገልጹ ሙሉ ቤተመጻሕፍት እና ሌሎች አስፈላጊ ቁሳቁሶችን በክልሎቹ ሙሉ ወጪ ለመሸፈን ቃል ገብተዋል ።

ዛሬ ስያሜ ያገኙት ትምህርት ቤቶች በጥቂት ቀናት ተጠናቀው ለትምህርት ዝግጁ እንደሚሆኑም ተገልጿል ።