አዲስ አበባ ፣ ህዳር 20 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ)የፌዴሬሽን ምክር ቤት የመከላከያ ሰራዊት ለተቀዳጀው ድል የእንኳን ደስ አላችሁ መልእክት አስተላለፈ፡፡
ምክር ቤቱ በደስታ መግለጫው የድል ስንደቅ የሀገር አለኝታና ደጀን የህዝብ ልጅ የሆነው ጀግናው የመከላከያ ሰራዊት በተቀዳጀው ድል የተሰማን ደስታ ስንገልፅ በከፍተኛ ኩራት ነውና እንኳን ደስ አላችሁ ፤ እንኳን ደስ አለን ብሏል፡፡
የመላው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ለጀግናው መከላከያ ሰራዊታችን በሞራል ፣ በሁለንተናዊ ድጋፎች ከጎኑ በመሆን ለተገኘው ድል ከፍተኛ ድርሻ አበርክታችኋል ነው ያለው።
ይህ ድል የሁላችንም የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ድል ነው ያለው ምክር ቤቱ ይህም የሕዝባችን ህብረ ብሄራዊ ጠንካራ አንድነት በጋራ የመቆም ውጤት እና የመከላከያ ሰራዊታችን የሕገ መንግስት ታማኝነት ድል መገለጫ ነው ሲል ገልጿል ።
የሀገር መከላከያ ሰራዊታችን ጀግንነት ፣ ምሳሌነት እና ቁርጠኝነት ለሀገራችን መፃዒ ጊዜያትም ትልቅ መሰረት እንደተከለ ምክር ቤታችን ይገነዘባል በማለትም በደስታ መግለጫው አስፍሯል።
ደስታውንና ድሉን እያጣጣምን በህብረ ብሄራዊ ፌዴራል ስርዓታችንና አብሮነታችንን የሚሸረሽሩ እኩይ ተግባራትን በተመሳሳይ መልኩ በጋራ እየተከላከልን ፤ አንድነታችን እና ክብራችንን አስጠብቀንና አጠናክረን ሀገራዊ ሁለንተናዊ ብልጽግና አጀንዳዎች ላይ በማተኮር የታላቅ ሀገር ባለቤትነታችንን በቀጣይ ድሎችም እናረጋግጣለን በማለትም ገልጿል።