ቢዝነስ

በመዲናዋ ባለፉት ስድስት ወራት የታደሰው የንግድ ስራ ፈቃድ  ከእቅዱ አንፃር ዝግተኛ መሆኑ ተገለፀ

By Tibebu Kebede

December 31, 2019

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 21፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ባለፉት ስድስት ወራት 347 ሺህ የንግድ ስራ ፈቃዶችን ለማደስ ታቅዶ ማደስ የተቻለው 197 ሺህ 254 የንግድ ስራ ፈቃዶች መሆኑን  የአዲስ አበባ ንግድና ኢንዱስትሪ  ቢሮ አስታወቀ፡፡

በአዲስ አበባ ንግድና ኢንዱስትሪ  ቢሮ የንግድ ስራ የንግድ ፍቃድ እና ምዝገባ ዳይሮክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ብርሀኑ ተግኝ  ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት ለእቅዱ አለመሳካት የኔትወርክ መቋራረጥ  የራሱ አስተዋፅኦ ነበረው፡፡

የንግድ ስራ ፍቃድ እና እድሳት ከሐምሌ አንድ ጅምሮ እስከ ታህሳስ 30 ያለቅጣት ማደስ የሚቻል ሲሆን ከጥር አንድ ጀምሮ ወደ ቅጣት እንደሚገባ ነው የተገለፀው፡፡

ከዚህ በፊት  የንግድ ማህበረሰቡ  ፍቃድ ባወጣበት ጽህፈት ቤት በመቅረብ እንዲያሳድስ ጥሪ ቀርቧል ተብሏል ።

በተጨማሪም የአስመጭና የላኪነት የንግድ ስራ ፈቃድ ከዚህ በፊት በፌዴራል ደረጃ ይሰጥ እንደነበር ያሰታወቁት ዳይሬክተሩ  በአሁን ወቅት ግን አዲስ አበባን ጨምሮ በ8 ክልሎች እየተሰጠ ይገኛል ብለዋል፡፡

በሲሳይ ጌትነት