አዲስ አበባ ፣ ህዳር 19 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የቢሾፍቱ – ጨፌ ዶንሳ – ሰንዳፋ የአስፋልት ኮንክሪት የመንገድ ግንባታ የአፈር ቆረጣ እና የውሃ መፋሰሻ ቱቦ የማምረት ስራዎች እየተከናወነ ይገኛል፡፡
መንገዱ የምስራቅ እና የሰሜን ሸዋን የሀገራችን ክፍሎችን በአቋራጭ የሚያስተሳስር ይሆናል፡፡
ፕሮጀክቱን በ941 ሚሊዮን ብር በሆነ ወጪ በመገንባት ላይ የሚገኘው ሀገር በቀሉ ራማ ኮንስትራክሽን ነው።
የትራንስፖርት ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ካሳሁን ጎፌ፣ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሃብታሙ ተገኘ እንዲሁም የተቋማቱ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች የመስክ የስራ ቅኘት አካሂደዋል።
ፐሮጀክቱ በ55 ኪ.ሜትር ርዝመት ቢሾፍቱ – ጨፌ ዶንሳ – ሰንዳፋን ያገናኛል፡፡
ዲዛይን እና ግንባታን በጋራ አካቶ የያዘው ፕሮጀክቱ በእስካሁኑ አፈጻጻም የተሰሩ ስራዎች፣ ያጋጠሙ ችግሮችና ቀጣይ የስራ እቅዶችን በተመለከተ ለተቋማቱ የስራ ሃላፊዎች ገለጻ ተደርጎላቸዋል።
በእስካሁኑ ክንውንም የካምፕ ግንባታ የመሬት ጠረጋ የአፈር ሙሌት ድልዳሎ ስራዎች እየተከናወኑ ነው።
የአፈር ቆረጣ እና የውሃ መፋሰሻ ቱቦ የማምረት ስራዎችም እየተከናወነ ይገኛል፡፡
የግንባታ ወጪው በኢትዮጵያ መንግስት የሚሸፈነው ይኸው ፕሮጀክት በርካታ እስትራቴጂካዊ ጠቄሜታዎች ያሉት በመሆኑ በ2015 በጀት አመት በወርሃ ህዳር በጊዜ ገድብ እንዲጠናቀቅ የስራ ሃላፊዎቹ አሳስበዋል።
የመንገዱን ግንባታ ጥራት በመቆጣጠር ረገድ ሲ-ደብሊው-ሲ-ኢ እና ጂ-ኤንድ-ዋይ የተባሉ አማካሪ ድርጅቶች ዮአሺን ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን ከተባለ የኮርያ ድርጅት ጋር በጥምረት የሚሰሩት ሲሆን ጥራትን በማስጠበቅ መንገዱ በተባለው ጊዜ እንዲጠናቀቅ አቅጣጫ መቀመጡን ከባለስልጣኑ ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡
የመንገዱ የጎን ስፋት በወረዳ ከተማ 21.5 ሜትር ፣ በቀበሌ 12 ሜትር እንዲሁም በገጠር 10 ሜትር ስፋት እንዲኖረው ተደርጎ ነው እየተገነባ የሚገኘው፡፡