አዲስ አበባ ፣ ህዳር 18 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሃይኮ ማስ ጋር ተገናኝተው በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳዮች እና የሁለትዮሽ ግንኙነት ዙሪያ ተወያዩ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለያዩ ሃገራት የነበራቸውን የስራ ተልዕኮ በዛሬው ዕለት አጠናቀዋል።
አቶ ደመቀ ተልዕኳቸውን አጠናቀው ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፉት ቀናት በተለያዩ የአፍሪካ እና የአውሮፓ ሃገራት ቆይታ አድርገዋል።
በዚህ ወቅትም መንግስት በትግራይ ክልል እየወሰደ ስላለው የህግ ማስከበር ዘመቻ ገለጻና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ከዚህ ባለፈም በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ከተለያዩ ሃገራት ተወካዮች ጋር ተወያይተዋል።
በጉብኝታቸው ወቅትም በአፍሪካ በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ በሩዋንዳ፣ ኬንያ እና ኡጋንዳ ጉብኝት በማድረግ ከሃገራቱ መሪዎች ጋር መክረዋል።
ከዚህ ባለፈም በአውሮፓ በጣሊያን፣ ቤልጂየም፣ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ እና ጀርመን ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን፥ ከመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋርም ተወያይተዋል።
በውይይታቸው ወቅትም በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ሰፋ ያለ ማብራሪያና ገለጻ አድርገዋል።
በተለይም መንግስት በትግራይ ክልል እየወሰደ ካለው ህግን የማስከበር ዘመቻ እና የሃገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ ገለጻ በማድረግ የመንግስትን አቋም ለየሃገራቱ አስረድተዋል።