አዲስ አበባ፣ ህዳር 18፣ 2013 (ኤፍቢሲ) በጠገዴ ወረዳ ቀራቅር መስመር ከህወሓት የጥፋት ቡድን ነጻ በወጡ አካባቢዎች የመንግስት ተቋማት አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል፤ ሕዝቡም ወደ ዕለት ተዕለት እንቅስቃሴው ተመልሷል።
ነፃ ከወጡት አካባቢዎች መካከል በከተማ ንጉስ፣ አዲ ረመፅና ቃፍታ ሁመራ አካባቢዎች የጥፋት ቡድኑ ተባባሪዎች እጃቸውን መስጠታቸውም ተነግሯል።
የቀራቅር ግንባር ቀጠና ኮማንድ ፖስት አስተባባሪ አቶ ብርሃኑ ተድላ በአካባቢዎቹ ሕዝቡን የማረጋጋት ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
አቶ ብርሃኑ “አጥፊው የህወሓት ቡድን በመከላከያ ሠራዊት ላይ ትንኮሳ ከፈጸመ በኋላ በአካባቢው ባሉ ወረዳዎች ያለው የፀጥታ መዋቅር ዝግጅት እንዲያደርግ ተደርጎ ነበር” ብለዋል።
በሠራዊቱ ላይ ጥቃት በተፈፀመበት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ሌሊት ዘጠኝ ሠዓት የጁንታው ተልዕኮ ፈጻሚዎች በጠገዴ ወረዳ በምትገኘው ቅራቅር ከተማ ላይ ጥቃት መሰንዘራቸውንም አስታውሰዋል።
የጥፋት ቡድኑ የቀራቅር ከተማን ለመቆጣጠር ‘ያለ የሌለ’ ኃይሉን መጠቀሙን የገለጹት አስተባባሪው በወቅቱ የአማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ ጥቃቱን መክቶ መቆየቱን ተናግረዋል።
በዚያው ዕለት በመከላከያ ሠራዊት የታገዘው የአካባቢው የፀጥታ ኃይል ቀራቅርን አስለቅቆ ከተማ ንጉስን በመቆጣጠር እስከ ቃፍታ ሁመራ ደርሷል ነው ያሉት።
ነፃ በወጡት አካባቢዎች የተቋቋመው ኮማንድ ፖስትም በቀበሌዎች ጊዜያዊ የሠላምና ደህንነት ኮሚቴ እያስመረጠ ሕዝቡን እያረጋጋ መቆየቱን ነው የገለጹት።
ከተሞችን ጨምሮ ካሉት 29 ቀበሌዎች ከአምስቱ በስተቀር ጊዜያዊ የሠላምና ደህንነት ኮሚቴ ተቋቁሟል ብለዋል።
በአካባቢዎቹ የነፍስ አድን ተቋማት የሚባሉት የውኃ፣ የጤናና ሌሎች መሰረታዊ አገልግሎቶች መጀመራቸውንም አቶ ብርሃኑ ተናግረዋል።
የመንግስት ሠራተኞችን በማወያየት ወደ ስራ የማስገባትና ሕዝቡንም የማረጋጋት እንቅስቃሴው መቀጠሉንም አክለዋል።
በአካባቢዎቹ ከጥፋት ቡድኑ ጋር ሄደው የነበሩና ጥፋት ሲፈጽሙ የቆዩ ግለሰቦች መንግስት ባስተላለፈው ጥሪ መሰረት እጃቸውን እየሰጡ መሆኑንም አስተባባሪው ገልጸዋል።
በየጫካው ተቆርጠው የቀሩ የጁንታው አባላት መኖራቸውን የጠቀሱት አቶ ብርሃኑ ያሉበት ቦታ ተለይቶ በፀጥታ ኃይል ክትትል እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።
በዚህ ሣምንት ስጋቶችን ሙሉ በሙሉ በማስወገድ ሕዝቡ ወደ ሠላማዊ እንቅስቃሴው እንዲመለስ የማድረግ ስራ ይሰራል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በአካባቢዎቹ የመማር ማስተማር ሂደትም በአጭር ጊዜ እንዲጀመር አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም አስታውቀዋል።