Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የህግ የበላይነትን ለማስፈን እየተወሰደ ያለው እርምጃ ተጠናክሮ ቀጥሏል –  የመተከል ዞን ኮማንድ ፖስት

አዲስ አበባ፣ ህዳር 18፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በመተከል ዞን እየተወሰደ ያለው ህግን የማስከበር ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የመተከል ዞን ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ ኮሎኔል አያሌው በየነ ገለጹ።

ካለፈው ሃምሌ ወር ጀምሮ እስካሁን 280 ጸረ ሰላም ሃይሎች ላይ እርምጃ መወሰዱንም ነው የገለጹት።

የጁንታውን ተልዕኮ በማስፈጸም በዞኑ ውስጥ ዜጎችን በመግደል፣ በማፈናቀልና ንብረት በማውደም የተሰማሩ ቡድኖችን ለማጽዳት እርምጃው ይቀጥላል ብለዋል ኮሎኔል አያሌው ።

ቀጠናው የአጎራባች ሃገራት አዋሳኝ ስለሆነ ለጠላት ሰርጎ ለመግባት አመቺ መሆኑና የጸረ ሰላም ሃይሎች ከህብረተሰቡ ጋር በመቀላቀላቸው ለይቶ ለማውጣት የአንዳንድ አመራሮች ቁርጠኝነት ማነስ ሁኔታውን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማረጋጋት አስቸጋሪ እንዳደረገውም ተናግረዋል።

ይሄን የጥፋት ተልዕኮ ለመደምሰስ የሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ የፌደራል ፖሊስና የክልሉ ልዩ ሃይል ፖሊስ በመቀናጀት የዘመቻ ስራዎች እየተከናወነ መሆኑን ገልጸው ህብረተሰቡ ጠላትን አጋልጦ እንዲሰጥ የፖለቲካ አመራሩ እየሰራ ይገኛልም ነው ያለው።

ቀጠናውን ወደ ነበረበት ሰላም ለመመለስ አጥፊዎችን በመደምሰስ እንዲሁም በጉዳዩ በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ የተሳተፉ አካላትን ወደ ህግ በማቅረብ የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡

ባለፉት ሁለት ቀናት ህግን ለማስከበር በተደረገው የተቀናጀ ዘመቻ በማንዱራ 17፣ በዳንጉር 4 እና በጉባ 2 በአጠቃላይ 23 ጸረ ሰላም ሃይሎች ላይ እርምጃ መወሰዱን ከመተከል ዞን ኮሙዩኒኬሽን ያገነነው መረጃ ያመለክታል፡፡

 

Exit mobile version