Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በእነ ጃዋር መሀመድ የክስ መዝገብ ተከሳሾች ባቀረቡት ቅሬታ ላይ ዐቃቤ ህግ የፅሁፍ መቃወሚያውን አቀረበ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 18፣ 2013 (ኤፍቢሲ) ዐቃቤ ህግ በእነ ጃዋር መሀመድ የክስ መዝገብ ተከሳሾች ባቀረቡት ቅሬታ ላይ የፅሁፍ መቃወሚያውን አቀረበ፡፡

የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 1ኛ የወንጀል ችሎት የዐቃቤ ህግን መቃወሚያ ለመስማት ለህዳር 18 ቀን 2013 ዓ.ም በሰጠው ቀጠሮ መሰረት ዐቃቤ ህግ መቃወሚያውን ለፍርድ ቤቱ አቅርቧል፡፡

በዚህ ችሎት ላይ ተከሳሾች አቶ ጀዋር መሀመድ እና አቶ በቀለ ገርባ ወደ ችሎቱ ያልቀረቡ ሲሆን ለዚህም፤ በሀገሪቱ ውስጥ ካለው ወቅታዊ ሁኔታ አንፃር እንዲሁም ባለን ፖለቲካዊ ተሳትፎ የተነሳ፣ በማረሚያ ቤቱ እና በፍርድ ቤት መካከል ያለው ርቀት ሰፊ በመሆኑ ሁኔታው የፀጥታ ስጋት ፈጥሮብናል ብለዋል፡፡

በዚህ ምክንያት መቅረብ አልቻልንም ያሉት ተከሳሾቹ በቀጣይ ለሚኖረው የፍርድ ሂደት “በአቅራቢያችን ጊዜያዊ ችሎት ይቋቋምልን” የሚል አቤቱታቸውን በጠበቆቻቸው በኩል በፅሁፍ አቅርበዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም ዐቃቤ ህግ 11ኛ ተከሳሽ አቶ ደጀኔ ጉተማ፣  14ኛ ተከሳሽ አቶ ብርሃነ መስቀል አበበ እና 15ኛ ተከሳሽ አቶ ፀጋዬ ረጋሳ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ለማድረግ በጋዜጣ ጥሪ ተደርጎላቸው ሊቀርቡ ስላልቻሉ በሌሉበት ክሳቸው እንዲታይ ትዕዛዝ እንዲሰጥበት ጠይቆ፤ ተከሳሾች በተቋሙ ላይ ላቀረቡት ቅሬታ በፅሁፍ ምላሽ መስጠቱን ገልጾ ነገር ግን ጠቅላይ ዐቃቤ ህጉ እንዲያቀርቡ የተፃፈ ትዕዛዝ ባለመኖሩ ሊቀርቡ አለመቻላቸውን አስረድቷል፡፡

የግራ ቀኙን ክርክር ያዳመጠው የፌደራል 1ኛ የፀረ ሽብርና ህገ-መንግስት ጉዳዮች ችሎት በጋዜጣ ጥሪ ተደርጎላቸው ያልተገኙ ተከሳሾችን በሚመለከት ክሳቸው በሌሉበት እንዲታይ ወስኗል፡፡

በሌላ በኩል እነ አቶ ጃዋር መሀመድ ያቀረቡትን ጊዜያዊ ችሎት ይቋቋምልን ጥያቄ ለፍርድ ቤቱ አስተዳደር አቅርቦ ምላሽ እንዲሰጥበት ያደርጋል ተብሏል፡፡

ጠቅላይ ዐቃቤ ህጉ በግለሰብ ደረጃ ቀርበው ምላሽ ይስጡበት ለሚለው የተከሳሾች ቅሬታ ላይ ትዕዛዝ ለመስጠት በሚዲያ ቀረበ የተባለው አስተያየት ቅጅው በእንግሊዝኛ እና አማርኛ በሲዲ ከቀረበ በኋላ ትዕዛዝ የሚሰጥበት መሆኑንም ገልጿል፡፡

ችሎቱ ለታህሳስ 8 ቀን 2013 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱን ከጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

 

Exit mobile version