ጤና

የእንቅልፍ ችግር ለከፋ የራስ ምታት በሽታ ያጋልጣል ተባለ

By Tibebu Kebede

December 31, 2019

አዲስ አበባ፣ታህሳስ 21፣2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የእንቅልፍ ችግር ለከፋ የራስ ምታት በሽታ ሊያጋልጥ እንደሚችል  አዲስ ጥናት አመልክቷል፡፡

የእንቅልፍ ሰዓት አጭር መሆንና ለመተኛት በሚሞከርበት ጊዜ ከእንቅልፍ በተደጋጋሚ  መንቃት  ለከፍተኛ የራስ ምታት በሽታ እንደሚያጋልጥ  በጥናት መታወቁን  በበርግሀም እና በቦስተን የሴቶች ሆስፒታል የእንቅልፍ ባለሙያ የሆኑት ዶክተር ሱዛን ቤርቼች ገልጸዋል፡፡

በዚህ ጥናት ቢያንስ ሁለቴ የራስ ምታት እንንዲሁም በወር ከ15 ጊዜ በታች የራስ ምታት የሚያጋጥማቸው 98 ሰዎች ተሳታፊ መሆናቸው ተነግሯል፡፡

ተመራማሪዎችም የእነዚህን ሰዎች የራስ ምታት ፣ የእንቅልፍ ሁኔታ እና የጤንነት ልማድ ለተከታታይ ስድስት ሳምንታት ክትትል አድርገዋል፡፡

በዚህ ወቅትም በሰዎቹ የእጅ አንጓ ላይ የእልቅልፍ ሁኔታቸውን የሚከታተል መሳሪያ ተገጥሞላቸው ቆይታል፡፡

በውጤቱም በእነዚህ ሰዎች ለስድስት ሳምንታት 870 የእራስ ምታት እንዳጋጠማቸው ተመራማሪዎቹ አስታውቀዋል፡፡

ተመራማሪዎቹ አክለውም በጥናታቸው እንደ ካፌይን ፣ አልኮሆል ፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እና ውጥረት  የመሳሰሉ ከፍተኛ የራስ ምታት መነሻ የሆኑ  ነገሮችን ካስተካከሉ በኋላ  በአንድ ሌሊት 6 ነጥብ 5 ሰዓታት ወይም ከዚያ ያነሰ እንቅልፍ ማግኘት  ወዲያውኑ ወይም በሚቀጥለው ቀን  ለሚከተሰት   መጥፎ የራስ ምታት ምክንያት  አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡

ሆኖም ግን በጥናቱ እንደተመለከተው የእንቅልፍ መዛባት በከፍተኛ የራስ ምታት ለመያዝ  ምክንያት እንደሚሆን ተመላክቷል፡፡

በእንቅልፍ  መዛባት  እና በከፍተኛ የራስ ምታት በሽታ መካከል ስላለው ግንኙነት የበለጠ ለማወቅ ተጨማሪ ምርምር  እንደሚያስፈልግ ተመራማሪዎቹ ገልጸዋል፡፡

ምንጭ፡-ዩ.ፒ.አይ