አዲስ አበባ ፣ ህዳር 17 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በያዝነው አመት ሰኔ ወር ላይ የመጀመሪያውን ዙር ሃይል ማመንጨት እንደሚጀም የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ አስታወቁ፡፡
ሚኒስትሩ ዩሲኤል ከተሰኘ የዩናይት ኪንግደም ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎችና ተማሪዎች ጋር የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ ተወካይ በተገኙበት ኢትዮጵያ በታዳሽ ሃይል ልማት ዘርፍ የምታከናውናቸውን ተግባራት በተመለከት ያላቸውን ልምድ አካፍለዋል፡፡
በኢትዮጵያ እና በምስራቅ አፍሪካ ሁለንተናዊ የኃይል አቅርቦትንና ሌሎች የእድገት ዓላማዎችን ለማሳካት የታዳሽ ኃይል ልማትን እንዴት ማፋጠን ይቻላል በሚል ሃሳብ ዙሪያ በቪዲዮ ኮንፈርንስ ተወያይተዋል፡፡
ሚኒስትሩ ልምዳቸውን እንዲያጋሩ የተጋበዙት በዘርፉ ከ30 ዓመታት በላይ የስራ ልምድና ከፍተኛ የሆነ የትምህርት ዝግጅት ያላቸው በመሆኑ ነው ተብሏል፡፡
በተጨማሪም ኢትዮጵያ ታዳሽ ኃይልን ለማጎልበት የምትሰራው ስራ ለሌሎች ሃገራት ምሳሌ የሚሆን በመሆኑ የዩኒቨርሲቲው ተመራማሪዎችና ተማሪዎች ከዚህ ልምድ እንዲቀስሙ ለማስቻል እንደሆነም ነው የተገለጸው፡፡
ሚኒስትሩም ኢትዮጰያውያን በመተባበር በራሳቸው ገንዘብ እየገነቡት የሚገኘው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ 5 ሺህ 150 ሜጋ ዋት ኃይል በማመንጨት ንጹህና ታዳሽ የሆነ የኤሌክትሪክ ሃይል ለዜጎች ለማቅረብ እንደሚያስችል ገልጸውላቸዋል፡፡
በተያዘው ዓመት ሰኔ ወር ላይም የመጀመሪያውን ዙር ኃይል ማመንጨት እንደሚጀምር አስታውቀዋል፡፡
በተጨማሪም ኢትዮጵያ ለራሷ ብቻ ሳይሆን ለምስራቅ አፍሪካ ሃገራት የንጹህና የታዳሽ ኃይል ምንጭ ቋት ለመሆን አቅዳ እየሰራች መሆኑንም አስረድተዋል፡፡