አዲስ አበባ፣ ህዳር 16፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) በግብፅ የኢትዮጵያ አምባሳደር ማርቆስ ተክሌ ግብፅ ካይሮ መቀመጫቸውን ላደረጉ የአፍሪካ ሀገራት አምባሳደሮች መንግስት እየወሰደ ስለሚገኘው ህግን የማስከበር እርምጃ በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በካይሮ ለሚገኙ ለተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት አምባሳደሮች መንግስት በትግራይ ክልል እየወሰደ ስለሚገኘው ህግን ማስከበር እርምጃ አስፈላጊነት አምባሳደር ማርቆስ ገለፃ አድርገዋል።
አምባሳደር ማርቆስ በማብራሪያቸው የፌዴራል መንግስት በህወሃት ውስጥ ካለው ቡድን ጋር ውይይቶችን ለማድረግ ተደጋጋሚ ሙከራ ቢያደርግም ሳይሳካላት መቅረቱን ተናግረዋል።
የሀገሪቱ መረጋጋት አደጋ ላይ መውደቁ መንግስት በትግራይ ክልል ህግን የማስከበር እርምጃውን እንዲጀምር እንዳስገደደው ጠቁመዋል።
አምባሳደር ማርቆስ እየተካሄደ የሚገኘው ህግን የማስከበር እርምጃ በህዳሴ ግድብ ዙሪያ እየተካሄደ በሚገኘው ውይይት ላይ ተፅዕኖ አያስከትልም ነው ያሉት።
ከህዳሴ ግድብ ጋር ተያይዞ ያሉ ችግሮችን በዲፕሎማሲ መንገድ ለመፍታት ኢትዮጵያ ቁርጠኛ መሆኗንም አምባሳደሩ መግለፃቸውን ኤምባሲው አስታውቋል።