አዲስ አበባ ፣ ህዳር 16 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ መንግሥት በጀመረው ህግ የማስከበር እርምጃ የአውሮፓ ህብረት በሃገሪቱ የውስጥ ጉዳይ ዙሪያ ጣልቃ የመግባት ፍላጎት እንደሌለው ገለፀ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከአውሮፓ ህብረት የአደጋ ስራ አመራር ኮሚሽነር ጃኔዝ ሌናርቺች ጋር በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ መክረዋል።
አቶ ደመቀ ኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ህግን ተፈፃሚ ለማድረግ ነባራዊ ሁኔታውን በማጥናት የሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽ የሚደረግበትን አግባብ አስረድተዋል።
አያይዘውም ንፁሃን ዜጎች ለከፋ ቀውስ ተጋላጭ እንዳይሆኑ እና የሰብዓዊ ድጋፍ በፍጥነት ተደራሽ እንዲሆን መንግሥት የጀመረው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
ኮሚሽነር ጃኔዝ ሌናርቺች በበኩላቸው÷ የኢትዮጵያ መንግሥት በጀመረው ህግን የማስከበር እርምጃ የአውሮፓ ህብረት በሃገሪቱ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ የመግባት ፍላጎት እንደሌለው ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ለህብረቱ ስትራቴጂያዊ አጋር ሃገር መሆኗንም ጠቅሰዋል።
በመሆኑም በህግ ማስከበር እንቅስቃሴ ለንፁሃን ዜጎች ሰብዓዊ ድጋፍ የሚሰጥበትን መንገድ ለማመቻቸት በመንግሥት የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ እንዲቀጥል መጠየቃቸውን ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።