አዲስ አበባ ፣ ህዳር 16፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ህወሓት በዓለም አቀፍ የጦር ወንጀልና የዘር ማጥፋት በመፈጸም ሊጠየቅ እንደሚገባ ምሁራን ገለጹ፡፡
ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉ የፌደራሊዝምና የግጭት አፈታት ምሁራን እንደገለጹት ቡድኑ በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎችም ሆነ በማይካድራ በፈጸማቸው ወንጀሎች ከተጠያቂነት አያመልጥም ሲሉ ነው የተናገሩት።
አሁንም ቢሆን በመቐለ የመሽገው ህወሓት ህዝቡን ለማስጨረስ ከሚያደርገው ድርጊት ሊታቀብ ይገባል ነው ያሉት።
ምሁራኑ የህወሓት ወቅታዊ አቋም የትግራይ ህዝብ ጉያ ውስጥ ተወሽቆ የማብቂያውን ሰዓት እየተመለከተ ነው ብለዋል።
ህዝብን ከአላስፈላጊ ጉዳት ለመታደግ ከመጣር እና ለህግና ስርዓት በሽንፈቱ እጅን ከመስጠት ይልቅ የጦርነት ትርክቱን ቀጥሎበታልም ብለዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፌደራሊዝም መምህርና የሰብዓዊ መብት ተመራማሪ ዶክተር ሲሳይ መንግስቴ የጁንታው ቡድን ከምስረታው ጀምሮ ቆሜለታለሁ ለሚለው የትግራይ ህዝብ የፈየደለት ነገር የለም ነው ያሉት።
በማብቂያው ዋዜማም ይህንኑ የታሪክ ሁነት እየደገመ ይገኛል ነው ያሉት ዶክተር ሲሳይ መንግስቴ።
በኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ በግጭት አፈታት ላይ ጥናት የሰሩት ዶክተር በቃሉ አጥናፉ ደግሞ የሀገር የመከላከያ ሰራዊት መቐለን መክበቡን ተከትሎ ህዝቡን ወደ እልቂት ለመምራት የቅስቀሳ ጥረቱን እንደቀጠለበት ጠቅሰዋል።
የታጠቀን የሀገር መከላከያ ሰራዊትን በቢላም ቢሆን ተዋጋ እያሉ መቀስቀስ በህዝብ ደም ለሰዓታትም ቢሆን በአምባገነንነት እስትንፋስን ለማቆየት ከሚደረግ መፍጨርጨር ጋር አመሳስለውታል።
ምሁራኑ የህልውና ዘመቻ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ እንኳን እየፈጸመ ባለው የጦር ወንጀል የጁንታው አባላት ለፍርድ ቀርበው ሊጠየቁ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በማይካድራ የተፈጸመውን የዘር ፍጅት በተመለከተ ያወጣውን ሪፖርት መነሻ ተደርጎም ተገቢውን ቅጣት ማግኘት ይኖርባቸዋል ሲሉም አክለዋል።
በሀገሪቱ የፍትህ ስርዓት በዚህ የጦር ወንጀል እና የሀገር ክህደት ከመጠየቅ እንደማያመልጡ የሚያውቁት የጁንታው አባላት አሁንም ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስበዋል።
ምሁራኑ ይህ ቡድን ካለፉት ጥፋቶቹ ባለመማር ዛሬም የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ይፈጽማል፤ የክልሉን ህዝብ መሰረተ ልማቶች እያወደመ እንደሚገኝም አንስተዋል።
ከጁንታው መሰሪና አደገኛ ባህሪያት አንጻር አጥፊና ለሚያናፍሳቸው ፕሮፓጋንዳዎች ጆሮን ሳይሰጥ ልዩ ኃይሉና ሚሊሻው በቃ ሊላቸው ይገባልም ነው ያሉት።
በኃይለየሱስ መኮንን