አዲስ አበባ ፣ ህዳር 16 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የህዝብ መተፋፈግን በመቀነስ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል ከአትክልት ተራ ተነስተው በጃን ሜዳ እንዲሰሩ የተደረጉ የአትክልት ነጋዴዎች በቅርብ ቀን ወደ ተዘጋጀላቸው የገበያ ማዕከላት እንደሚዛወሩ ተገለጸ።
የአዲስ አበባ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በፌስ ቡክ ገጻቸው ላይ÷ ዛሬ ማለዳ በከተማዋ በግንባታ ላይ ያሉ እና ተገንብተው ያለ አገልግሎት የተቀመጡ የገበያ ማዕከላትን መጎብኘታቸውን አስታውቀዋል።
በሃይሌ ጋርመንት፣ በጀሞ አደባባይ አካባቢ፣ ኮልፌ እና በሌሎችም አካባቢዎች በተደረገ ጉብኘት ግንባታዎቹ ያሉበትን ደረጃ እና ጥራት መገምገማቸውንም ጠቅሰዋል።
እንደ አዲስ የተገነቡና ነባር የገበያ ማዕከላት እድሳታቸው ተጠናቆ ቅድሚያ በጃን ሜዳ ላሉ የአትክልት ተራ ነጋዴዎች እንዲሰጡ ይደረጋልም ነው ያሉት።
አያይዘውም ለስራ ክፍት ሲሆኑ ለአምራች ፣ ለነጋዴ እና ለሸማቹ የተሻለ የገበያ አቅርቦትና ትስስር ይፈጥራሉም ብለዋል።
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።