አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 21፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የብስክሌት ትራንስፖርት አገልግሎት የሙከራ ትግበራን በይፋ ጀመረ።
በመንገድ ትራንስፖርት አገልግሎት ዘርፍ ውስጥ ከሚጠቀሱ የትራንስፖርት ዓይነቶች የሞተር አልባ ትራንስፖርት አንዱ ሲሆን፥ በዋናነት ከሚጠቀሱት ውስጥ የብስክሌት ትራንስፖርት ይገኝበታል።
በድሬዳዋ ከተማ ጤናማ እና አማራጭ የትራንስፖርት አገልግሎት ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ ያለመ የብስክሌት ትራንስፖርት የሙከራ ትግበራ በዛሬው ዕለት ተጀምሯል።
አገልግሎቱን የትራንስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሙሉ ገብረእግዚአብሔር፣ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ አህመድ ቡህ፣ የፌዴራል ትራንስፖርት ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዱልበር ሸምሱ እና ሌሎች የስራ ኃላፊዎች በይፋ አስጀምረውታል።
የትራንስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሙሉ ገብረእግዚአብሔር እና ምክትል ከንቲባ አቶ አህመድ ቡህ የብስክሌት የትራንስፖርት አገልግሎቱን በዘላቂነት ለማስቀጠል የፌዴራል መንግስት ፣ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ሴክተር መስሪያ ቤቶች እና መንግስታዊ ያልሆኑ በጎ አድራጊ ድርጅቶች የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህም የሞተር አልባ ትራንስፖርት አገልግሎቶችን በተመረጡ አምስት የሃገሪቱ የተለያዩ ከተሞች ለማስጀመር ወደተግባር ተገብቷል።
ከአነዚህም ከተሞች ውስጥ ድሬዳዋ፣ አዲስ አበባ፣ ባህር ዳር፣ መቀሌ እና ሃዋሳ እንደሚገኙበት ከትራንስፖርት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
የብስክሌት ትራንስፖርት አገልግሎቱ ቀደም ብሎ በአዲስ አበባ ከተማ ተጀምሮ የነበረ ቢሆንም ብዙም ስኬታማ መሆን እንዳልቻለ ይታወሳል።