Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ምክትል ጠ/ሚ ደመቀ መኮንን ከአውሮፓ ህብረት ምክትል ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ቦሬል ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 16 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከአውሮፓ ህብረት ምክትል ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ቦሬል ጋር ተወያይተዋል።

አቶ ደመቀ ወደ ቤልጅየም በማቅናት ለጆሴፍ ቦሬል በኢትዮጵያ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ ገለፃ አድርገዋል።

ወንበዴው የህውሓት ቡድን በየጊዜው የሚፈጽመው ዘግናኝ ጥፋት ሃገሪቷን እና ቀጠናውን ወደለየለት ትርምስ ሊስገባው እንደነበር አስታውሰዋል።

በተለይም የወንበዴው የህውሓት ቡድን የፈፀማቸው ፍፁም አረመኔያዊ ድርጊቶች ትክክለኛውን ገፅታ ለመረዳት የቅርብ ጊዜውን የማይካድራ ጭፍጨፋ ለአብነት በመጥቀስ የቡድኑን የክፋት ጥግ አስረድተዋል።

በአሁኑ ወቅትም የሃገር እና የህዝብን ህልውና ለማስጠበቅ መንግስት ህግ የማስከበር እርምጃ በመውሰድ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ መድረሱን መግለፃቸውን ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍ እንዲያገኙ በሚያስችል በጥንቃቄ እና ሃላፊነት በተሞላበት አግባብ አስፈላጊው ሁሉ ይከናወናልም ነው ያሉት፡፡

በመሰረታዊነት አጀንዳው የሃገሪቱ የውስጥ ጉዳይ በመሆኑ ያለማንም ጣልቃ ገብነት በሉዓላዊነት ላይ ለተጋረጠ ፈተና መንግስት የጀመረው ህግን የማስከበር እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

Exit mobile version