Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ሰራዊቱ አክሱም ከተማ በመግባቱ አካባቢው እየተረጋጋ ነው – የአክሱም ነዋሪዎች

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 16 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የመከላከያ ሠራዊት አክሱም ከተማ በመግባቱ አካባቢው እየተረጋጋ መሆኑን የከተማዋ ነዋሪዎች ተናገሩ።

ነዋሪዎቹ በከተማዋ የተቋረጠው መብራትና ሌሎች አገልግሎቶች በአፋጣኝ እንዲጀመሩላቸው ጠይቀዋል።

የሀገር መከላከያ ሰራዊት አክሱም ከተማን ከጁንታው ታጣቂ ነፃ በማድረግ ከተቆጣጠረ በኋላ በአካባቢው የነበሩ ስጋቶች እየቀነሱ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ተጀምሯል።

የተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች በስፍራው ተገኝተው የከተማዋን አንቅስቃሴ ተመልክተዋል።

በከተማዋ ቀደም ሲል የህወሓት ጁንታ ሲያናፍሰው በነበረው የሀሰት ዘመቻ ተረብሸው የነበሩ ነዋሪዎች አሁን ላይ ተረጋግተዋል።

የህወሓት ጁንታ ነዋሪዎችን “ወራሪ መጣባችሁ፣ ለመዋጋት ተዘጋጁ” በማለት በአክሱም ሲለፍፍ እንደነበርም በርካቶች ያስታወሱታል።

የሀገር መከላከያ ሰራዊት አክሱምን ከተቆጣጠረ ጀምሮ ግን ህዝብን በማረጋጋት፣ ሰላምና ፀጥታን በመጠበቅ፣ አለኝታነቱንና የህዝብ ወገንተኝነቱን አሳይቶናል ብለዋል ነዋሪዎቹ።

ሰራዊቱ የከተማዋን ሰላምና ፀጥታ የህዝቡን ደህንነት በማስጠበቅ ረገድ ሳይታክት እየሰራ መሆኑንም ነዋሪዎቹ ገልጸዋል።

በመሆኑም አክሱም አሁን ላይ እየተረጋጋችና ከነበረው ውጥረት ተላቃ “ትንፋሽ አግኝታለች” ነው ያሉት።

እንደ አስተያየት ሰጭዎቹ ገለፃ በከተማዋ የተቋረጠው የባንክ፣ የመብራትና ሌሎችም አገልግሎቶች ቶሎ እልባት እንዲያገኝ ፍላጎታቸው መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል።

በተለይ በከተማዋ ያለው ከፍተኛ የውሃ ችግር እንዲፈታ መንግስት የተቻለውን ሁሉ ጥረት እንዲያደርግም ነው የጠየቁት፡፡
ከተማዋ ይበልጥ እንድትረጋጋና የነዋሪው ችግር እልባት እንዲያገኝ ህዝቡ በመንግስት የሚተላለፉ መልዕክቶችን በመተግበር እገዛ ማድረግ ይጠበቅበታል ነው ያሉት።

የከተማዋ ነዋሪዎች ከሀገር መከላከያ ሰራዊት ጋር በመተባበር የህግ ማስከበር ስራ እንዲሳካ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማድረግም ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

Exit mobile version