አዲስ አበባ ፣ ህዳር 16 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በሰሜን ምዕራብ ግንባር ከዳንሻ እስከ አድዋ በነበረ አውደ ውጊያ የጁንታው ኃይል ከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ኪሳራ ደርሶበታል።
በዚህ ውጊያ ከ10 ሺህ በላይ የጁንታው ሀይል መደምሰሳቸውን እና ከ15 ሺህ በላይ የነፍስ ወከፍ፣ የቡድን እና ከባድ መሳሪያዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የግንባሩ ሚዲያ አስተባባሪ ኮሎኔል አባተ ንጋቱ አስታውቀዋል።
ጀግናው የመከላከያ ሠራዊት በርካታ ኪሎ ሜትሮችን በእግሩ አልፎ እና በተሽከርካሪ 24 ሰአት ተጉዞ ለዚህ ድል በቅቷል ብለዋል።
የጁንታው ሀይል ተቆጣጥሯቸው የነበሩ ከፍተኛ የጦር መሳሪያ መጋዘኖች እና እስከ 4 ዙር የገነባቸው ከባድ ምሽጎች ከ20 ደቂቃ ባልበለጡ ውጊያዎች መደምሰሳቸውንም ተናግረዋል።
በሺዎች የሚቆጠሩ የጁንታው አባላት እጃቸውን መስጠታቸውንም ነው የገለጹት ፡፡
ከሽሬ አለፍ ብሎ በለስ በተባለ ቦታ በ4 ዙር ተቆፍሮ የነበረ የጁንታውን ምሽግ የህገወጡ ህወሓት አመራሮች ደብረፅዮን እና ስብሀት ነጋ በቦታው ተገኝተው መርቀውት እንደነበር እና ሰራዊታቸውን ለማነቃቃት መከላከያን እዚህ እንቀብረዋለን ብለው ቢናገሩም ሲመኩበት የነበረ ምሽግ በ20 ደቂቃ ውጊያ ተደምስሷል ማለታቸውን አብመድ ዘግቧል።