አዲስ አበባ ፣ ህዳር 16 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ሃገራት በሌሎች የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ያለመግባት መርህን ሊያከብሩ እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አሳሰቡ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ረጅም የሀገረ መንግስት ታሪክ ያላት ሃገር መሆኗን በመጥቀስ ከመጀመሪያዎቹ የመንግስታቱ ድርጅት ማህበር አባል ሃገር እና አንደኛዋ መስራች መሆኗንም አውስተዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም አፍሪካ ህብረት ጠንሳሽና መስራች መሆኗን አስታውሰዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለባለብዙ ወገን ትብብር እና ለዓለም አቀፍ ህግጋት መርሆዎችና ህጎች ላይ ጠንካራ የሆነ የማይናወጥ የረጅም ጊዜ ታሪክ ያላት ሃገር ስለመሆኗም አውስተዋል፡፡
እንዲሁም በተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ሰላም ለማስከበር ከተሰማሩ ወገኖች መካከል በርካቶችን በቀዳሚነት ማበርከቷንም ጠቅሰዋል፡፡
ከተባበሩት መንግስታት ዋነኛ ህግጋት ውስጥ በአንቀጽ 2 (7) ላይ እንደሚደነግገው ማንኛውም ሃገር በአንድ ሉዓላዊ ሃገር ላይ ጣልቃ ስላለመግባት ይደነግጋል፡፡ የዓለም አቀፍ ፍርድ ቤትም ይህንን ጉዳይ አጽንኦት በመስጠት አንድ ሉዓላዊ ሀገር የውስጥ ጉዳዩን ያለማንም ጣልቃ ገብነት የማካሄድ መብትን ያረጋግጣል፡፡ እነዚህ መርሆዎች ከአፍሪካ ህብረት ህግጋት ውስጥ የሚመነጩም ናቸው፡፡
ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አሁን መንግስት እያካሄደ ያለውን ህግ የማስከበር ዘመቻ ለማገዝ ያሳየውን ፍላጎት ያደንቃል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህ በዓለም አቀፍ ሕግጋት መሠረት መከናወን እንዳለበት ለማስገንዘብ እንወዳለንም ብለዋል፡፡
ይህም የኢትዮጵያ መንግስት ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጥያቄዎችን እስከሚያቀርብ ድረስ ከጎኑ ሊቆሙ እንደሚገባ አጽንዖት ይሰጣልም ነው ያሉት፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት በፈረንጆቹ 2018 አጠቃላይ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሲጀምሩ ጥምር የሰላምና የብልጽግና አላማዎችን በሀገሪቱ ለማስፈን ተነሳስተው መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
ከፖለቲካ እና ከኢኮኖሚ ማሻሻያ በኋላ ይህንን ሰላምና የብልጽግና ጉዞ ለመቀልበስ የተለያዩ ኃይሎች ሙከራ አድርገዋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ በተለይም አብዛኛውን ነገር በቁጥጥሩ ስር አድርጎ የነበረው ህወሓት የተሃድሶውን ሂደት በመሸርሸር እና በኃይል በመጠቀም እራሳቸውን ወደስልጣን ለማምጣት ሞክረዋል ብለዋል፡፡
የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ማሻሻያ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ህወሓት የዴሞክራሲ ሂደቱን ለማደናቀፍ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ውስጥ የሚኖሩ እና ባሉበት አካባቢ በቁጥራቸው አነስተኛ የሆኑትን በእምነትና በዘር በመለየት ለማጥቃት የተለያዩ ወገኖችን በማሰልጠን በማስታጠቅ እና የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ጥቃቶችን ሲፈጽም መቆየቱንም አስታውሰዋል፡፡
በተጨማሪም ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ሰሜን ዕዝ በሚገኘው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ላይ ጨለማን ተገን አድርጎ ጥቃት ፈጽሟልም ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡
ጥቃቱንም በእርሱና ከሠራዊቱ ውስጥ በነበሩ ቅጥረኛ ከሃዲዎች ጭምር በመታገዝ የተፈጸመ ስለመሆኑንም ነው ያነሱት፡፡
ይህንን ጉዳይ ስለመፈጸማቸውም በግልጽ በሰሜን ዕዝ ላይ “መብረቃዊ ጥቃት” ፈጽመናል ሲሉ ተናግረዋልም ነው ያሉት፡፡
ይህ ስልጣንን ህገመንግስታዊ ባልሆነ መንገድ በኃይል ለመንጠቅ የሚደረግ ግልጽ ተግባር መሆኑንም በማውሳትም የሃገሪቱ ህግ የማይፈቅደው የወንጀል ድርጊት ስለመሆኑም አስገንዝበዋል፡፡
ህወሓት በቅርቡም በማይካድራ 600 ንጹኃን ዜጎችን ጨፍጭፏል፤ በዚህ አሰቃቂ ድርጊት ዙሪያ የመጀመሪያውን የአምነስቲ ሪፖርት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ያረጋገጠው ሲሆን በህወሓት የተፈጸመው ጭፍጨፋ በሰው ልጆች ላይ የተቃጣ እና የጦር ወንጀል ስለመሆኑም አስረድተዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ሉዓላዊነቱን ለማስከበር እና ከሃዲዎችን ወደ ፍርድ ለማምጣት ህግ የማስከበር ዘመቻውን የጀመረው በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ ስለመሆኑንም አብራርተዋል፡፡
እንደ አንድ ሉዓላዊ ሀገር ኢትዮጵያ የራሷን የውስጥ ውስጥ ጉዳይ በራሷ ህግጋት እየተመራች የማስፈጸም ሙሉ መብት ያላት ሀገር ስለመሆኗ በመጥቀስም አሁን እየተደረገ ያለውም ይህ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
በሰሜን የሀገሪቱ ክፍል እየተካሄደ የሚገኘው ህግ የማስከበር ዘመቻ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማዕቀፍ ውስጥ በመሆን መንግስት ንጹኃን ዜጎች በማይጎዱበት መልኩ እየተከናወነ ስለመሆኑም ነው የገለጹት፡፡
ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ውስጥ የሚገኙ ወዳጅ ሃገራት ያሳዩትን መቆርቆር ታደንቃለች ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ በሀገሪቱ ህግና ዓለም አቀፍ መርሆዎች ላይ በመመስረት አሁን የተፈጠረውን ሁኔታ ኢትዮጵያ በራሷ ለመፍታት አቅሙ እንዳላት ላስገነዝብ እወዳለሁም ብለዋል፡፡
አያይዘውም “የወዳጅ ሀገራት ምክርን ብንገነዘብም በውስጥ ጉዳያችን ላይ ጣልቃ እንዲገቡ ፍቃዳችን አይደለም” ነው ያሉት፡፡
ስለሆነም “ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ከጣልቃ ገብነት እንዲቆጠብና በዓለም አቀፍ ህግ መሰረት ጣልቃ ያለመግባት መሰረታዊ መርሆዎችን እንዲያከብሩ በአክብሮት እናሳስባለን” ብለዋል በመልዕክታቸው፡፡