አዲስ አበባ ፣ ህዳር 15 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ)በአርባ ምንጭ ከተማ በተከሰተ የትራፊክ አደጋ የ9 ሰዎች ህይወት ማለፉን የዞኑ ፓሊስ መምሪያ ገለፀ፡፡
የዞኑ ፓሊስ አዛዥ ኮማንደር ረታ ተክሉ እንደገለፁት÷ ዛሬ ከረፋዱ 4:00 አካባቢ ከአርባምንጭ ወደ ኮንኮ ሲጓዝ የነበረ ሚኒባስ መኪና ከአርባምንጭ ከተማ መውጫ በሚገኘው ቁልቁለት መንገድ ስቶ ወደ ገደል በመግባቱ አደጋው መከሰቱን ገልጸዋል።
በአደጋው 7 ወንድ እና 2 ሴት በአጠቃላይ 9 ሰዎች ህይወት ወዲያውኑ ያለፈ ሲሆን ÷ በሌሎች 5 ሰዎች ላይ ከባድ የአካል ጉዳት መድረሱንም ተናግረዋል።
በህይወት የተረፉ ሰዎች ጉዳት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መሆኑን የጠቆሙት ኮማንደር ረታ÷ ይህም የሞት መጠኑን እንዲጨምር ሊያደርግ ይችላል ነው ያሉት ፡፡
ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች ህይወት ለመታደግ አስፈላጊው ህክምና በአርባምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል በመሰጠት ላይ መሆኑን ገልፀው፣ የአደጋውን መንስኤ የፖሊስ አደጋ መርማሪ ግብረ ኃይል በማጣራት ላይ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ