Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ኢትዮጵያ እና ቻይና ለጋራ ብልፅግና አብረው የሚሰሩ አጋሮች

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 15 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያና ቻይና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመሩበትን 50ኛ ዓመት በተለያዩ ስነ ስርዓቶች በማክበር ላይ ይገኛሉ።

የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ይ ጋር የ50ኛ ዓመት የወዳጅነት በዓሉን አስመልክተው “ኢትዮጵያና ቻይና ለጋራ ብልፅግና አብረው የሚሰሩ አጋሮች” በሚል ርዕስ የሁለቱን ሀገራት የ50 ዓመታት ወዳጅነት የሚያትት ፅሁፍ በጋራ አዘጋጅተዋል።

በጽሁፋቸውም ኢትዮጵያ እና ቻይና የሁለቱን ሀገራት ቀደምት ስልጣኔ አንድ ላይ ያጣመረውን ይፋዊ የዲፕሎማሲ ግንኙነት በፈረንጆቹ 1970 በዛሬዋ እለት ህዳር 15 ቀን መጀመራቸውን አስታውሰዋል።

የሀገራቱ ግንኙነት 50 ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን፥ ባለፉት 50 ዓመታት በዓለማችን ላይ በርካታ ለውጦች ቢከሰቱም ሁለቱ ሀገራት በእነዚህ ዓመታት በእኩልነት፣ በመከባበር እና አንዱ የአንዱን ፍላጎትና እድገት በመደገፍ፣ በመረዳዳትና በማክበር እንዲሁም በጋራ በመሆን ዘርፈ ብዙ ግንኙነቶችን ሲያካሂዱ መቆየታቸውንም ገልፀዋል።

ሁሉን አቀፍ የሆነው የሁለቱ ሀገራት ስትራቴጂካዊ ግንኙነት እያደገ መጥቶ አሁን ላይ ከምንጊዜውም በተለየ መልኩ ጠንካራ መሰረት ላይ የቆመ መሆኑንም አትተዋል።

ሀገራቱ በፖለቲካው ዘርፍ ያላቸው የሁለትዮሽ መተማመን እና አጋርነትም እየጠነከረ መምጣቱን በማንሳት፤ የሁለቱ ሀገራት መሪዎች ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ በተለያየ ጊዜ በይፋዊ ስብሰባ፣ በስልክ እና በቪዲዮ ኮንፈረንስ ተከታታይ ውይይቶችን ማድረጋቸውን በጽሁፉ አውስተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድም በፈረንጆቹ 2018 በቤጂንግ በተካሄደው የቻይና አፍሪካ ጉባዔ ላይ እንዲሁም በ2019 በተካሄደው ቤልት ኤንድ ሮድ ትብብር ጉባዔ ላይ በተሳተፉበት ወቅት በቤጂንግ ጉብኝት ማድረጋቸውንም ጽሁፉ አስታውሷል።

በቀደሙት ጊዜያትም አፄ ኃይለስላሴ በማኦ ዜዶንግ ዘመን ቻይናን የጎበኙ ሲሆን፥ ከዚያ በኋላ የነበሩ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትሮችም በተደጋጋሚ በቻይና ጉብኝት ማድረጋቸውና ከቻይና መሪዎች ጋር በቅርበት ሲሰሩ እንደነበረም ተጠቅሷል።

ከዚህ በዘለለም ሀገራቱ በአየር ንብረት ለውጥ፣ የድህነት ቅነሳ እና በቀጠናዊ ግጭቶች ዙሪያ ከተባበሩት መንግስታት እና ከሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በመተባበር ሲሰሩ መቆየታቸውም ይታወቃል ብሏል ጽሁፉ።

በትብብር መስክም ባለፉት 50 ዓመታት ኢትዮጵያ እና ቻይና ውጤት ማስመዝገባቸውን የሚያትተው ጽሁፉ፥ ቻይና የኢትዮጵያ ትልቋ የንግድ፣ የኢንቨስትመንት ምንጭ እና የልማት አጋር መሆኗንም አመላክቷል።

በፈረንጆቹ ከ2000 እስከ 2019 ባለው ጊዜ ብቻ የሀገራቱ የባለሁለት መንገድ የንግድ መጠንም በ26 እጥፍ እድገት ማሳየቱ በማሳያነት ተቀምጧል።

የኢትዮጵያ ቡና እና አበባ በቻይና ገበያዎች ላይ ከፍተኛ ተቀባይነት ያለው ሲሆን፥ ከኢትዮጵያ ወደ ቻይና የሚላከው የሰሊጥ ምርትም የሀገሪቱን የሰሊጥ ፍጆታ 1/10 የሚሸፍን ነው ተብሏል።

በአንፃሩ የቻይና ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ጠቅላላ ዋጋቸው ከ1 ነጥብ 153 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ የሚያወጡ ከ1 ሺህ 500 በላይ ፕሮጀክቶች ላይ እየተሳተፉ ሲሆን፥ በዚህም በኢትዮጵያ ከ60 ሺህ በላይ የስራ እድል መፍጠር መቻሉም ተገልጿል።

ኢትዮጵያ የቻይና ሮድ ኤንድ ቤልት ትብብር ማዕቀፍን ከፈረሙ የአፍሪካ ሀገራት ውስጥ ቀዳሚዋ ስትሆን፥ የአዲስ አበባ ጂቡቲ የባቡር መንገድ ግንባታም የዚሁ ትብብር ማሳያ ተደርጎ እንደሚጠቀስም ተመላክቷል።

የመንገዶች፣ የአውሮፕላን ማረፊያዎች፣ የኢንዱስትሪ ዞኖች፣ የኤሌክትሪክ ሀይል እና ሌሎች መሰረተ ልማት ግንባታዎች እንዲሁም በቻይና አጋዥነት ኢትዮጵያ ያመጠቀቻት ETRSS-1 የመሬት ምልከታ ሳተላይት እና በቻይና ድጋፍ የተካሄደው የአዲስ አበባ የወንዞች ዳርቻ ፕሮጀክት የሁለቱ ሀገራት ትብብር የደረሰበትን ደረጃ የሚያሳይ መሆናቸውም ታውቋል።

ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት በተሻለ መልኩ በቻይና በርካታ መዳረሻዎች ያለው የኢትዮጵያ አየር መንገድም የሰዎችን ዝውውር በማቀላጠፍ እና የሚሰጠውን የጭነት አገልግሎት በማሳለጥ በአፍሪካ እና በቻይና መካከል  ድልድይ ሆኖ እያገለገለ መሆኑም የሁለቱ ሀገራት የተጠናከረ ግንኙነት ማሳያ ሆኖ ቀርቧል።

በጤናው መስክም ሀገራቱ በርካታ ስራዎችን በአጋርነት ሲሰሩ መቆየታቸው የተነሳ ሲሆን፥ በቅርብ ጊዜ እንኳን ኮቪድ19 በመከላከሉ ረገድ ቻይና እና ኢትዮጵያ ስኬታማ ትብብር ማድረጋቸው ተጠቅሷል።

በዚህ ረገድም የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለቻይና አጋርነታቸውን የሚያሳይ ደብዳቤ መላካቸውን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ ስልክ በመደወል ጭምር አጋርነታቸወን ማረጋገጣቸውን ጽሁፉ አንስቷል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በኮቪድ 19 ወረርሽን ወቅት ወደ ቻይና በረራ ባለማቋረጥ ቫይረሱን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ውስጥ የተለያዩ የህክምና እና ሌሎች መሳሪያዎችን በማጓጓዝ ቁልፍ ሚና መጫወቱም ተጠቅሷል።

የቻይና መንግስት እና የቻይና ተቋማት የኮቪድ19 ወረርሽኝ መከሰትን ተከትሎም በርካታ የህክምና እና ሌሎች የቫይረሱ መከላከያዎችን ለኢትዮጵያ ማበርከታቸውን፣ የቻይና የህክምና ልዑክ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ልምድ ማካፈሉ እና ሌሎችም በማሳያነት ተጠቅሰዋል።

በቀጣይም ኢትዮጵያ እና ቻይና በቤጂንግ የቻይና አፍሪካ የትብብር ጉባዔ መሰረት የቤልት ኤንድ ሮድ ትብብርን ለማጠናከር የሁለትዮሽ ግንኙነቱን የበለጠ ለማጠናከር የሚሰራ መሆኑም በጽሁፉ ተነስቷል።

እንዲሁም በመሰረተ ልማት፣ በኢንዱስትሪ ዞን፣ በቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን፣ በዘመናዊ ግብርና፣ በቱሪዝም እና በሃይል ልማት ዘርፍ በጋራ የሚሰራ ሲሆን፥ በዚህም የኢትዮጵያ እና የቻይና ትብብር የቻይና አፍሪካ ትብብር እና የሮድ ኤንድ ቤልት ትብብር ምሳሌ ለማድረግ እንደሚሰራም በጽሁፉ ተመላክቷል።

የሀገራቱን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትም በጤና፣ በትምህርት፣ በባህል እና በቱሪዝም ዘርፍ በማጠናከር እንደሚሰራ እና በዚህም የኢትዮጵያ እና የቻይና ወዳጅነት ህዝባዊ መሰረት እና ድጋፍ ያለው እንደሚደረግም ተገልጿል።

ግማሽ ክፍለ ዘመንን ያስቆጠረው የኢትዮጵያ እና የቻይና ግንኙነት አሁን ታሪካዊ ምእራፍ ላይ መድረሱን ያመላከተው ጽሁፉ፥ ሀገራቱ በሁሉም ዘርፍ ያላቸውን ትብብር ለሁለቱ ሀገራት እና ህዝቦች የተሻለ ነገ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጧል።

Exit mobile version