Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

“ልጆቻችን ሰኞ አስታጥቀው ማክሰኞ ለግዳጅ ዝመቱ አሏቸው፤ ዳሩ ግን በሰላም እጅ ሰጥተው ከእጃችን ገብተዋል” – ወ/ሮ ድንቅነሽ አድሃኖም

አዲስ አበባ፣ ህዳር 14፣ 2013 (ኤፍቢሲ) በደቡባዊ ትግራይ ዞን የዛታ ከተማ ነዋሪዋ እናት ወታደር ሲያዩ ልጆቼ ይሏቸዋል፡፡

የወንድ ልጆች እናት ናቸውና የጦርነት ውጣ ውረድ ከአንጀታቸው ገብቶ ያንሰፈስፋቸዋል፡፡

የበሬ ግምባር በምታክል ትንሽ ከተማ ውስጥ አውራ ጎዳና ዳር ወጥተው ወጭ ወራጁን ከንፈራቸውን እየመጠጡ ይመለከታሉ፡፡

ህግ ለማስከበር ከታች ላይ የሚለው የሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ የአማራ ልዩ ኃይል እና ሚሊሻ የሚባል መለያ ቢኖረውም ለእርሳቸው ግን ሁሉም ወጥቶ-አደሮች ናቸው፡፡

በደረታቸው ሲሳቡ፣ ወድቀው ሲነሱ፣ ጥይት በጭንቅላታቸው ላይ ሲያፏጭ ከሦስት አስርት ዓመታት በኋላ ዳግም ትናንት በማየታቸው ቅስማቸው በሃዘን ተሰብሯል፡፡

እመት ድንቅነሽ አድሃኖም በደቡባዊ ትግራይ ዞን በዛታ ወረዳ ዛታ ከተማ ነዋሪ ናቸው፡፡

እመት ድንቅነሽ ጦርነትን በታሪክ ሰምተውት ሳይሆን በተግባር ተፈትነውበት ያውቁታል፡፡

ልጄዋ! ያኔ ኮረም ከተማ ውስጥ ነዋሪ ነበርኩ አሉ፤ በ1983 ዓ.ም ገደማ መሆኑ ነው፡፡

በገባችበት በር ልትወጣ ቋፍ ላይ የቆመው ህወኃት “ፊታውራሪ ነኝ” የምትልበት፣ “ብሶት የወለደን ነን” ብለው ገብተው የቀጣዩ ትውልድ የብሶት ምንጭ የሆኑበት ያ አስከፊ ጦርነት የእመት ድንቅነሽን ርህራሄ በብርቱው ፈትኖት አልፏል፡፡

ሰባት ቁስለኛ ቤታቸው ውስጥ አስተኝተው ለፈውሳቸው ምክንያት ሆነዋል፡፡

“በሌሊት ተነስቸ ውሃ የምንቀዳበት ምንጭ ሩቅ ነበርና ሁለት ማዲጋ ውሃ አመጣላቸዋለሁ” ያሉኝ እናት ድንቅነሽ አንዱን ማዲጋ ውሃ ለቁስላቸው ማጠቢያ፤ ሌላኛውን ደግሞ ለመጠጣቸው ያውሉታል፡፡

እንደዛሬው ጉልበታቸው ሳይደክም ጠላ ጠምቀው እና ሽጠው ልጅ ያሳደጉት እናት ከልጆቻቸው ሌላ የደስታቸው ምንጭ የያኔውን ፈተና ያለሃዘን መሻገራቸው ነበር፡፡

ከዚያ በኋላ ለፈጣሪ የሚቀርብ የዘወትር ልመናቸውም “ጦርነትን ዳግም አታሳየኝ!” ቢሆንም ይህው ዛሬ ደግሞ ሲድህ በቀያቸው ደርሶ አዩት፡፡

ያኔ አባቶቻቸውን በጦርነቱ ምክንያት ያጡ በርካታ ልጆች ያለአባት እንዳደጉ እመት ድንቅነሽ ህያው ምስክር ናቸው፤ የነዛ ልጆች አስከፊ የህይዎት ገፅታ ለአሁኖቹ ህፃናትም ደርሶ ባያዩ እንደሚወዱ እንባ ባዘለ ዓይናቸው ሲናገሩ ሃዘናቸው ጥልቅ መሆኑ ይጋባል፡፡

ያለፈውን ዘመን ብሶት እና ጉዳት አስበው “ጦሱን ይዞ ይሂድ” የሚሉት እናት ድንቅነሽ ከጦርነት ዋዜማ ጀምሮ ያልተወቃ የጤፍ ነዶ በመኪና ጭነው መውሰዳቸውን እንኳን “ለጤና ያድርግላቸው” ብለዋቸዋል፡፡

“ልጄዋ! እንደክፉ አሳባቸው እና ጅማሯቸው ምህረቱ የሚማረር አይደለም” ብለዋል እናት ድንቅነሽ፤ ከዚህ ሁሉ ግፍ በኋላ እንኳን አንደበታቸው ፈጣሪያቸውን ከማመስገን አልዛለም፤ የጦርነቱ ቅድመ ዝግጅት እና ጥድፊያ አካባቢውን አሸብሮት እንደነበር ነግረውናል፡፡

“ልጆቻችን ሰኞ አስታጥቀው ማክሰኞ ለግዳጅ ዝመቱ አሏቸው፤ ዳሩ ግን በሰላም እጅ ሰጥተው ከእጃችን ገብተዋል” ብለዋል፡፡

የረዘመ ጊዜ ያልወሰደው የአካባቢው ጦርነት ተጠናቆ የሰላም አየር ባገኙባት ሁለት ቀናትም ተገደው የታጠቁ የአካባቢው ሚሊሻዎች ትጥቅ እየፈቱ በሰላም መግባታቸው ትንሽ እፎይታን ሰጥቷቸዋል፡፡

የእመት ድንቅነሽ ፀሎትም በሰፈራቸው የሚያዩቸው ወታደሮች በሰላም ወደ የአካባቢያቸው እንዲገቡ ነው እና የትውልድ ቀያቸው ኮረም እንደ ዛታ ነፃ ሆና ማየት ነው፡፡

የእናቶች ልመና የአባቶች ፀሎት እና የጥምር ጦሩ ብርታት የእመት ድንቅነሽን እና የኢትዮጵያዊያንን ጭንቀት አቃሎ ሰላም የምናይበት ጊዜ ሩቅ አይደለም ሲል የዘገበው አብመድ ነው፡፡

 

Exit mobile version