የሀገር ውስጥ ዜና

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ ከአሜሪካ አምባሳደር ጋር ተወያዩ

By Tibebu Kebede

December 30, 2019

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 20 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ማይክል ራይነር ጋር ተወያዩ።

በውይይታቸውም በሁለትዮሽና ቀጠናዊ ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል።

አቶ ገዱ በዚህ ወቅት እንደገለፁት በኢትዮጵያና በአሜሪካ መካከል ያለው ታሪካዊና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የሁለቱን ሃገራት የጋራ ጥቅም ከማስጠበቅ አንፃር ለዘመናት የዘለቀ ነው።

አሜሪካ በኢትዮጵያ በትምህርት፣ በጤና፣ በሰብዓዊ ልማት እና በሌሎች ዘርፎች እያደረገች ያለውን ድጋፍም አድንቀዋል።

ሁለቱ ሃገራት በቀጠናው ሰላም እንዲሰፍን በበርካታ ጉዳዮች በትብብር እየሰሩ መሆኑን ጠቅሰው፥ ይህንኑ አጠናከሮ ለማስቀጠል በሁሉም ወገን በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ማይክል ራይነር በበኩላቸው በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን ሁሉን አቀፍ ለውጥ አድንቀው፥ ኢትዮጵያ በቀጠናው እያደረገች ላለው አስተዋጽኦ አሜሪካ ያላትን አድናቆት ገልጸዋል።

ሃገራቸው በኢትዮጵያ የተጀመረው ለውጥ ግቡን እንዲመታ ድጋፏን አጠናከራ ትቀጥላለችም ብለዋል።

የሁለቱን ሃገራት ህዝቦች ጥቅም ለማስጠበቅ አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ መናገራቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።